የጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ ሼክ ሀሰን የበሬ ኮምፕሬሄንሲቭ ሆስፒታል ከለውጡ በፊት ታካሚዎችን ለእንግልት ሲዳርግ የቆየውን የአገልግሎት አሰጣጥ በመሰረታዊነት የቀየሩ ስራዎችን አሁን እውን አድርጓል ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገልጸዋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ከከፍተኛ የመንግስት ስራ ኃላፊዎች ጋር የጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ ሼክ ሀሰን የበሬ ኮምፕሬሄንሲቭ ሆስፒታል የለውጥ ስራዎችን ጎብኝተዋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገፃቸው ባሰፈሩት መልእክት፣ ሆስፒታሉ ከለውጡ በፊት ታካሚዎችን ለእንግልት ሲዳርግ የቆየውን የአገልግሎት አሰጣጥ በመሰረታዊነት የቀየረ ስራዎችን አሁን እውን አድርጓል ብላዋል።
በተለይ ለታካሚዎች የሚሰጠውን አገልግሎት የሚያዘምኑ የጤና መሠረተ ልማቶችን በማሟላት ሰፊ አገልግሎትን እየሰጠ እንደሚገኝም ተመልክተዋል።
ሆስፒታሉ የተለያዩ የህክምና አገልግሎቶችና ዘመናዊ የህክምና ቁሳቁሶችን በማሟላት ለተጠቃሚው የህብረተሰብ ክፍል ደረጃውን የጠበቀ እና ጥራት ያለው የህክምና አገልግሎት ለመስጠት ሰፊ የአገልግሎት ማሻሻያና የማስፋፊያ ሥራዎችን አከናውኗል ብለዋል።
የሆስፒታሉ አረንጓዴ ምድረ ግቢ ለህክምና አገልግሎት የሚመችና ፅዱ የሥራ ከባቢ እንዲፈጠር አድርጓል።
በሌላ በኩል በጅግጅጋ ከተማ ሁሉን አቀፍ እንዲሁም ዘመኑን የዋጀ የተቋም ግንባታን እያከናወኑ የሚገኙትን የሶማሌ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን እና የብልፅግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤትን ማየታቸውን አስታውቀዋል፡፡
ተቋማቱ በሰው ኃይል፣ በቴክኖሎጂና በቢሮ እድሳት አስደናቂ ለውጥ ላይ እንደሚገኙም መመልከታቸውን ገልፀዋል፡፡