ኢትዮጵያውያን ከዓድዋ እስከ ሕዳሴው ግድብ ያሉ ድሎችን በአብሮነት እንዳሳኩት ሁሉ ለቀጣይ ሀገራዊ ድሎችም መተባበር እንዳለባቸው ተመላክቷል
ዓድዋ ጥበብ ነው፤ የማይረሳ ታሪክ በሀገር ልጆች ጀግንነትና ጥበብ የተገለጠበት፣ ዓድዋ እውነት ነው፤ ውሸት በአደባባይ የተረታችበት፡፡ ዓድዋ አብሮነት ነው፤ ሁሉም ለሀገር ክብር በአንድነት የቆመበት፡፡ ዓድዋ ቅኔ ነው፤ ሰው ሞቶ ሰው ሊያድን ልክ እንደ ሰርገኛ ሆ! ብሎ የዘመተበት፡፡
የበርካታ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ህዝቦች መኖሪያ፣ የብዝሃ ቋንቋ፣ ባህልና መልክዓ ምድር ባለቤት የሆነችው ኢትዮጵያ ይህ ብዝሃነት ትልቅ ሀብት ሆኗት ዜጎቿ በመሰባሰብ የዓድዋን ድል ተጎናፅፈዋል፡፡ ታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብም በጋራ ገንብተዋል። ወደፊትም እነዚህን አሰባሳቢና የወል ትርክት በማጉላት አንድነትን ማጠናከር ላይ አተኩሮ መስራት ይገባል፤ ይላሉ በዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህር ሳሙኤል ሺበሺ፡፡
በዓለማችን ይህን መሰል ብዝሃነት ያለባቸው ሀገራት ልዩነታቸውን በአንድነት አስተሳስረው በመያዛቸው ሁለንተናዊ ለውጥ ማስመዝገብ መቻላቸውን አውስተው፣ ለአብነትም ህንድን ምሳሌ በማድረግ ጠቅሰዋል።
“ህንድ በርካታ ብሔረሰቦችን፣ ቋንቋዎችና ባህሎችን የታደለች ሀገር ናት፡፡ ከፍተኛ የህዝብ ቁጥርም አላት፡፡ አልፎ አልፎ የእርስ በርስ አለመግባባቶች ቢኖሩም ከልዩነት ባሻገር አንድ የሚያደርጉ የወልና አሰባሳቢ ትርክትን በመገንባት ሀገራዊ አንድነቷን አጠናክራ መቀጠል ችላለች” ብለዋል፡፡
አክለውም፣ በህንድ ለሁሉም ብሔሮች፣ ዕምነቶች፣ ቋንቋዎች እና ባህሎች ክብርና እውቅና በመሰጠቱ በህንዳውያን ዘንድ ተከባብሮና አብሮ መኖር አንዱ እሴት ሆኖ እንዲቀጥል ማድረጓን ገልፀዋል፡፡
እንደ መምህር ሳሙኤል ገለፃ፣ አንዱ የሌላውን ባህልና ማንነት ማወቅና ማክበር፣ ከልዩነት ይልቅ ለአንድነት ከፍ ያለውን ዋጋ መስጠት እና በጋራ ትርክት ላይ ማተኮር አንዱ የህዝቦች ማሰባሰቢያና የጋራ ሀገርን መገንቢያ መንገድ ስለመሆኑም ተናግረዋል፡፡
ኢትዮጵያም ሰፊ የተፈጥሮና ማህበራዊ ካፒታል የሆነ ድንቅ ብዝሃነት ያላት ሀገር ናት፡፡ ምንም እንኳን በየዘመናቱ የተወሰኑ መንሸራተቶች ቢኖርም እነዚህን የተፈጥሮ፣ ባህላዊ እና ኃይማኖታዊ ልዩነቶች አቻችሎ የመኖር ልምድ አለ። ለአብነትም እንግዳን ተቀብሎ መኝታን ሳይቀር ለቅቆ ማሳደር፣ ማብላትና ማጠጣት፣ ደስታና ሀዘንን እኩል ተጋርቶ ማሳለፍ የመሳሰሉ ባህሎች አሉ፡፡
ሊያስተሳስሩ የሚችሉ ነገሮችን እንደ ዕድል አለመጠቀም እንደ ሀገር አንዱ ማነቆ እንደሆነ የተናገሩት መምህር ሳሙኤል፣ አሁንም ቢሆን ኢትዮጵያውያንን በብርቱ ሊያስተሳስሩ የሚችሉ የወልና አሰባሳቢ ትርክት ገንብቶ እንደ ዓድዋ ለዓለም የሚበቃ፣ እንደ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብም ሀገርና አህጉርን የሚያነቃ፣ ብዙ ድሎችን በአብሮነት የምናስመዘግብባቸው ዕድሎች አሉ ብለዋል፡፡
ከዘመናዊው ባሻገር በየአካባቢው ያሉ ባህላዊ የግጭት ማጥፊያ ጥበቦችን፣ የስራ ባህሎችን፣ የማህበራዊ መስተጋብርን፣ መረዳዳትን እና መጠያየቅን የሚያጎለብቱ እሴቶችን ለህብረ ብሔራዊነት መጎልበት፣ ለሀገራዊ ድልና ስኬቶች የበለጠ መጠቀም እንደሚገባም ገልፀዋል፡፡
መምህር ሳሙኤል፣ ልዩነትን ለመራራቂያ ሳይሆን ለውበት መጠቀም ላይ በሚገባ መስራት እንደሚገባ ገልፀው፣ ይህንንም ከቤተሰብ፣ ከአካባቢና ከትምህርት ቤት ጀምሮ ትውልዱ ላይ ወጥነትና ተከታታይነት ያላቸውን ተግባራት መከወን ያስፈልጋል። ከተናጠልና ከሀሰት ትርክት በመውጣት አስተሳሳሪ በሆኑት ላይ መስራት ይገባልም ብለዋል፡፡
እንደ ሀገር ከለውጡ ወዲህ የወልና አሰባሳቢ ትርክትን ለመገንባት እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት ተስፋ ሰጪ መሆናቸውን ጠቅሰው፣ ለአብነትም የዓድዋ ድል መታሰቢያ መገንባትን ማሳያ አድርገዋል። መታሰቢያው የወልና አሰባሳቢ ትርክትን ለመገንባት የሚደረገውን ጥረት የሚያግዝ ስለመሆኑም አንስተዋል፡፡
የወል ትርክት ለወል ሀገር አስፈላጊ መሆኑን የገለፁት መምህር ሳሙኤል፣ በሚያለያዩ ትርክቶች ላይ ከመጠመድ ይልቅ በሚያቀራርቡ ጉዳዮችና ሀገራዊ ተስፋዎች ላይ ማተኮር ለጋራ ሀገራዊ ዕጣ ፈንታችን ብሩህነት መሠረት ነው።
የወል እሳቤን ማደርጀት፣ ለወል ሀገር ግንባታ መሠረት በመሆኑ እንደ ዓድዋ ድል መታሰቢያ አይነት የእሴት ግንባታ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባውም ተናግረዋል፡፡
የወልና አሰባሳቢ ትርክትን ለመገንባት ከሚደረገው ጥረት ባልተናነሰ መልኩ አስተሳሳሪ እና ሁሉንም ማዕከል ያደረጉ ልማቶችም መገንባት እንዳለባቸው የገለፁት መምህሩ፣ እንደ ህዳሴው ግድብ የመሳሰሉ አስተሳሳሪ ልማቶችን አቅም በፈቀደ መልኩ መተግበር ሀገራዊ አንድነትን በፅኑ መሰረት ላይ ለመገንባት ትልቅ መሰረት የሚጥል ስለመሆኑም ጠቁመዋል፡፡
በሐሮማያ ዩኒቨርሲቲ የታሪክና ቅርስ አስተዳደር ትምህርት ክፍል መምህር ተማም ሐጅአደም (ዶ/ር) ለአዲስ ልሳን ጋዜጣ እንደገለፁት ኢትዮጵያ ብዙ አሰባሳቢ ትርክት አሏት፡፡ ለአብነትም የዓድዋ ድል አንዱ ነው። በዚህ ዘመን ደግሞ እንደ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ አይነት ታላላቅ ፕሮጀክቶችን መጥቀስ እንችላለን ብለዋል፡፡
በተለይም የዓድዋ ድል የኢትዮጵያውያን አብሮነት ጎልቶ ከሚወሳባቸው የታሪክ ምዕራፎች መካከል አንዱ ነው ይላሉ ተማም ሐጅአደም (ዶ/ር) ምክንያቱን ሲያስረዱም፣ “የዓድዋ ድል ሁሉም የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ህዝቦች በእምነት፣ በባህል እና በቋንቋ ሳይለያዩ ከሁሉም አቅጣጫ መጥተው የተሳተፉበትና ታላቅ መስዋዕትነት ከፍለው ያገኙት ድል ነው። ድሉ ኢትዮጵያውያን ለጋራ ዓላማ የተነሱበትና ነፃነታቸውን ያስጠበቁበት ነው፡፡ የህዳሴው ግድብም የኢትዮጵያውያን ህብረት በተግባር የተገለፀበት ታላቅ ድል እንደሆነም አንስተዋል፡፡
የዓድዋ ድልም ሆነ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ህብረ ብሔራዊነት መገለጫችን፣ አብሮነታችን ያለውን ታላቅነት የሚያመላክቱ ናቸው። በተለይም የዓድዋ ድል ኢትዮጵያ በሁሉም ዜጎቿ ተጋድሎ የፀናች ሀገር መሆኗን መስካሪ ነው፡፡ የተማረው፣ ያልተማረው፣ ገበሬው፣ ወንድና ሴቱ…. ሁሉም የተሳተፉበት ነው፡፡ ይህም አንዱ ያለ ሌላው መኖር እንደማይችል የሚያሳይ ነው፡፡ ደስታና ድልን፣ ሀዘንና ችግርን በጋራ ተካፍሎ መቆምን የሚያሳይ ነው ብለዋል ተማም (ዶ/ር)፡፡
ዋና መስሪያ ቤቱን በአሜሪካ ያደረገውና በመላው ዓለም የተለያዩ የጥናት ውጤቶችን በማሳተም የሚታወቀው ካሪ ጆርናል “ለጋራ ድሎች ተገቢውን ዋጋ መስጠት ሀገራዊ አንድነትን ለማጠናከር ያለው ፋይዳ” በሚል ርዕስ እ.ኤ.አ መጋቢት 27 ቀን 2023 ይፋ ባደረገው ጥናት መሰረት፣ ጥቂት የማይባሉ የዓለማችን ሀገራት ለጋራ ድሎቻቸው ቦታ በመስጠታቸው ጠንካራ ሀገር መገንባት ችለዋል፤ ንቁ ማህበረሰብ በመፍጠርም ኢኮኖሚያቸውን አሳድገዋል፡፡
እንደ ጥናቱ ከሆነ የጋራ ታሪክ ሀገራዊ አንድነትን ያሳድጋል፤ የጋራ ታሪካዊ ትውስታን በዜጎች ልቦና ውስጥ ያስቀምጣል፤ በህብረተሰብ መካከል ሰላማዊ ግንኙነትን በመፍጠር የሀገር ግንባታ ሂደትን ከፍ የሚያደርጉ ዜጎችን በማፍራት ረገድም ወሳኝ ሚና ይጫወታል።
ታሪክ በህብረተሰብ ዕድገት እና ውህደት መካከል አዎንታዊ ግንኙነት አለው። ይህንንም እውን ለማድረግ ያለፈው ትውልድ የገነባቸውን መልካም ታሪካዊ እሴቶች እና ቅርሶችን ማስተዋወቅ እንደሚገባ የታሪክ ምሁራን ይናገራሉ፡፡
በጥናቱ መሠረት፣ ወደፊት ለመራመድ ምርጡ መንገድ ታሪክን ወደ ኋላ መመልከት ነው። ታሪክ ህብረተሰቡ ከየት እንደመጣ፣ ያጋጠሙት ተግዳሮቶች ምን ምን እንደሆኑ፤ እነዚህንም ለመፍታት ምን አይነት ብልሃትን እንደተጠቀመ፣ የቱ እንደተሳካለት፣ የትኛው ለምን እንደከበደው በተጨባጭ የሚያስተምር ነው፡፡
ለጋራ ታሪክ የሚገባውን ክብር መስጠት በአንድ ሀገር የዜጎችን ንቃተ ህሊና ማዳበር፣ የሀገር ፍቅርን ከፍ ማድረግ፣ በጥቃቅን ጉዳዮች ሀገራዊ ዋልታዎችን የማይንድ ትውልድን መገንባት እንደሚቻል ከላይ በጠቀስነው ጥናታዊ ሰነድ ተመላክቷል፡፡ በዓለማችን ገናና ታሪክ ካላቸው ሀገራት መካከል ኢትዮጵያ ከቀዳሚዎቹ ተርታ እንደምትሰለፍ የታሪክ ድርሳናት ይመሰክራሉ።
ከቅርብ ጊዜ ታሪካችን አንድ እውነት ብንመዝዝ እንኳ ታላቁን የዓድዋ ድል እናገኛለን። የህዳሴውን ግድብ የመሳሰሉም በጋራ ቆመን ገድል ያስመዘገብንባቸው እና የህብረ ብሔራዊነታችን መገለጫ እና የአንድነታችን ፅኑ ማረጋገጫ የሆኑ መሰል ድሎች አሉን፡፡
ከዚህ ባሻገርም ሀዘንና ደስታችን በጋራ የምንካፈልባቸው ባህላዊ ክንዋኔዎች እና መሰል እሴቶች አሰባሳቢ ትርክትን ለመፍጠር እንደሚያግዙም ምሁራኑ ይናገራሉ፡፡
በርግጥም ኢትዮጵያ ድንቅ ነች፡፡ እንደ ዳሎል በፍፁም ትህትና ዝቅ ብላ ሁሉንም የምታከብር ደግሞም እንደ ዳሽን ተራራ ከፍ ብላ በኩራት የጀግንነቷን እና የነፃነት ተሟጋችነቷን የሚመሰክሩ ታሪኮቿን የምትናገር ቅኔ የሆነች ሀገር ናት፡፡
ደጋ፣ ወይና ደጋ፣ ቆላና በርሃ ልዩ ልዩ የአየር ንብረት ያለባት አይነግቡ ምድር፤ ጠይም፣ የቀይ ዳማው፣ ጥቁርና ቀዩ ሁሉም በየመልኩ የሚኖርባት ግሩም ሀገር መሆኗን ብዙዎች በየዘመናቱ ቢመሰክሩላትም ይህንን ሀብቷን በወጉ ገልጣ፣ አልምታና አስተዋውቃ በተገቢው አለመጠቀሟን እየጠቀሱም ብዙዎች ቁጭታቸውን ይሰነዝራሉ፡፡
የታሪክ ምሁራኑ ዓድዋ ሦስት አበይት ነገሮችን ያስተምረናል ይላሉ፡፡ ይሄውም ውስጣዊ አንድነትን ማጠናከር፣ ዘመኑ የሚፈልገውን ዕውቀትና ቴክኖሎጅ መታጠቅ እና ጠንካራ የዲፕሎማሲ ስራ መስራት እንደሆነም ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ የታሪክ ጉዞ እንደሚነግረን በዚህ ሀገር ታሪክ ከፍታ ውስጥ ሁሉም ኢትዮጵያዊ በህብር የሚችለውን ጡብ ማስቀመጡን ያወሱት የፖለቲካል ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህር ሳሙኤል ሺበሺ (ዶ/ር) ሁሌም የጋራ ለሆነው ድል በጋራ መቆም እና ለሀገር የሚጠቅሙና ዘመኑን የዋጁ ተጨማሪ ድሎችን ማስመዝገብ ያሻል ሲሉ ተናግረዋል፡፡
በመለሰ ተሰጋ