የኢትዮጵያ የኒውክሌር ቴክኖሎጂ ልማት ለሰላማዊ አገልግሎት ብቻ ጥቅም ላይ የሚውል ነው

You are currently viewing የኢትዮጵያ  የኒውክሌር ቴክኖሎጂ ልማት ለሰላማዊ አገልግሎት ብቻ ጥቅም ላይ የሚውል ነው

AMN ህዳር 29/2018

የኢትዮጵያ የኒውክሌር ቴክኖሎጂ ልማት መርሃ ግብር ለሰላማዊ አገልግሎት ብቻ ጥቅም ላይ የሚውል መሆኑን የኢትዮጵያ የኒውክሌር ኢነርጂ ኮሚሽን ኮሚሽነር ሳንዶካን ደበበ ገለጹ።

የኢትዮጵያን የኒውክሌር ኃይል ልማት መርሃ ግብር ማስጀመሪያና የኢትዮጵያ የኒውክሌር ኃይል ኮሚሽን ሥራ ማስጀመሪያ የምክክር መድረክ በመካሄድ ላይ ይገኛል።

በመድረኩ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ(ዶ/ር)፣ የኢትዮጵያ የኒውክሌር ኢነርጂ ኮሚሽን ኮሚሽነር ሳንዶካን ደበበ፣ የዓለም አቀፍ አቶሚክ ኢነርጂ ኤጀንሲ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ሚካኤል ቹዳኮቭ እና የባለድርሻ ተቋማት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ የኒውክሌር ኢነርጂ ኮሚሽነር ሳንዶካን ደበበ በዚሁ መድረክ ላይ፤ የኢትዮጵያ የኒውክሌር ቴክኖሎጂ ልማት የኃይል ደህንነትን በማረጋገጥ የኢኮኖሚያዊ ሽግግርና የረጅም ጊዜ የመቋቋም አቅም ግንባታ ላይ የተመሠረተ ብሔራዊ የልማት ተነሻሽነት ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ሰላማዊ የኒውክሌር ቴክኖሎጂም ንጹህ የኃይል አቅርቦት የማመንጨት አቅምን በማላቅ የጤና፣ የግብርና እና የኢንዱስትሪ እንዲሁም የምርምር ትግበራ ማዕቀፍ የተቃኘ መሆኑን ገልጸዋል።

የሰላማዊ አማራጭ የኒውክሌር ሳይንስ ልማት መርሃ ግብሩም የኢትዮጵያውያንን ህይወት በተጨባጭ የሚያሻሽሉ ጥቅሞችን የሚያስገኝ ዕድል ማረጋገጥ እንደሆነም ተናግረዋል።

የኃይል አቅርቦት የዕድገት ሞተር ነው ያሉት ኮሚሽነሩ የሰላማዊ አማራጭ አስተማማኝ የኒውክሌር ኃይል ልማት መርሃ ግብርም የኢትዮጵያን ዕድገት ጥራትና ፍጥነት ይቀርፃል ብለዋል።

የኢትዮጵያ መንግሥት የኒውክሌር ኃይል ልማት ቁርጠኝነትም ቀጣይነት ያለው የኢኮኖሚ ዕድገትን ማረጋገጥን ታሳቢ ያደረገ ውሳኔ መሆኑን አብራርተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ምረቃ ላይ በጉባ ከመበሰሩ ማግስት በሩሲያ የተካሄደው ዓለም አቀፍ የአቶሚክ ኃይል መድረክ ድረስ ኢትዮጵያ ለሰላማዊ የኒውክሌር ልማት ያላትን ቁርጠኝነት ማረጋገጣቸውን አስታውሰዋል።

በዚህም ኢትዮጵያ የኒውክሌር ቴክኖሎጂን ለሰላማዊ አገልግሎት ብቻ ለመጠቀም ሙሉ በሙሉ ቁርጠኛ ነች ብለዋል።

የኢትዮጵያ የኒውክሌር ኃይል ኮሚሽን በተሰጠው ግልጽ ሥልጣንና በተፈጠረለት ጠንካራ መዋቅር ከዓለም አቀፍ የአቶሚክ ኢነርጂ ጋር በቁርጠኝነት እንደሚሰራ ገልጸዋል።

የዓለም አቀፍ አቶሚክ ኢነርጂ ኤጀንሲ ጋር የተፈጠረው የሥልጠና ፕሮግራምና የባለሙያ የልምድ ልውውጥ፣ ክህሎት ግንባታና የቴክኒክ ትብብር የኮሚሽኑን ስራ እያሳለጠ መሆኑንም ተናግረዋል።

በቀጣይም ኢትዮጵያ በዕውቀትና በሰላማዊ የኒውክሌር ልማት የጋራ ርዕይ በመመስረት ከዓለም አቀፍ አቶሚክ ኢነርጂ ኤጀንሲ ጋር የትብብር ስራን አጠናክራ እንደምትቀጥል ማረጋገጣቸዉን ተዘግቧል፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review