በ3ኛው የደረጃዎች ቦርድ ስብሰባ የፀደቁ አስገዳጅ ደረጃዎች በጥብቅ ክትትል ተፈፃሚ እንደሚሆኑ የኢትዮጵያ ደረጃዎች ኢንስቲትዮት አስታወቀ።
ኢንስቲትዮቱ ታህሳስ 3/2018 ዓ/ም ባካሄደው በ3ኛው የደረጃዎች ቦርድ ስብሰባ የፀደቁ 84 አስገዳጅ ደረጃዎችን በተመለከተ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል።
ጋዜጣዊ መግለጫውን የሰጡት የኢትዮጵያ ደረጃዎች ኢንስቲትዮት ዋና ዳይሬክተር መሰረት በቀለ (ዶ/ር)፤ የፀደቁ 84 አስገዳጅ ደረጃዎች በኬሚካልና የኬሚካል ውጤቶች፣ በኤሌክትሮ ሜካኒካል፣ በኮንስትራክሽንና በተፈጥሮ ጋዝ ዘርፎች ላይ ያተኮሩ ናቸው ብለዋል።
እነዚህ ደረጃዎች በአስገዳጅነት እንዲፀድቁ የተደረጉት የሀገርን ኢኮኖሚ መሰረት ባደረገ መልኩ የህብረተሰብን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ሲሆን፤ በተለይም ምርቶች ጥራታቸውን እንዲመጥኑ ለማድረግ መሆኑን ዋና ዳይሬክተሯ አብራርተዋል።

የነበሩና አዲስ ደረጃዎች የፀደቁበት ሂደት የነበሩ ህጎችን ክለሳ በማድረግ፣ ለቁጥጥር አመች ካልሆነና ምርቶቹ ጊዜውን እንዲዋጁ ለማድረግና የአዳዲስ ዘርፎችን ደረጃ ለማውጣት መሆኑን መሰረት (ዶ/ር) ገልፀዋል።
የሀገር ውስጥ ምርቶች ተወዳዳሪና ተመራጭ እንዲሆኑ እንደዚህ አይነት ደረጃዎች ወሳኝ መሆናቸውን የጠቀሱት የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር፤ ለተግባራዊነታቸው ሁሉም ባለድርሻ የበኩሉን እንዲወጣ አሳስበዋል።
የኢትዮጵያ ደረጃዎች ኢንስቲትዮት የህዝብ ግንኙነትና ኮሚኒኬሽን ስራ አስፈፃሚ አቶ ብሩክ ሐብቴ በበኩላቸው፤ እነዚህ ደረጃዎች ሲፀድቁ በየዘርፉ ያሉ ከፍተኛ ባለሙያዎችና የቴክኒክ ኮሚቴዎች ተገምግመው የፀደቁ መሆናቸውን ተናግረዋል።

የፀደቁ አስገዳጅ ደረጃዎች ከዛሬ ጀምሮ ተግባራዊ እንደሚሆኑ በመግለጫው ተመላክቷል።
በንጉሱ በቃሉ