ታይምስ ኦፍ ኢንዲያ የኢትዮጵያ እና የሕንድ ስትራቴጂካዊ ወዳጅነት አዲስ ከፍታ ላይ መድረሱን ዘገበ

You are currently viewing ታይምስ ኦፍ ኢንዲያ የኢትዮጵያ እና የሕንድ ስትራቴጂካዊ ወዳጅነት አዲስ ከፍታ ላይ መድረሱን ዘገበ

AMN ታኅሣሥ 11/2018 ዓ.ም

ታዋቂው የሕንድ ጋዜጣ “ታይምስ ኦፍ ኢንዲያ” ኢትዮጵያ እና ሕንድ በ2025 በታሪካቸው ታይቶ የማይታወቅ ስትራቴጂካዊ ትስስር ውስጥ መግባታቸውንና “መንፈሳዊ አጋሮች” (Strategic Soulmates) መሆናቸውን ዘግቧል።

ጋዜጣው ባወጣው ትንታኔ፣ ሁለቱ ሀገራት በታሪክ፣ በባሕልና በጂኦ-ፖለቲካ ያላቸው ቁርኝት አሁን ላይ ወደ ላቀ የኢኮኖሚና የቴክኖሎጂ ሽርክና ማደጉን ገልጿል።

ይህን ዘገባ ያጠናከረችው ታዋቂዋ የሕንድ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች፣ ደራሲ እና የስትራቴጂክ ጉዳዮች ተንታኝ ራሽሚ አናንድ (ረዳት ፕሮፌሰር) ስትሆን፣ ጸሐፊዋ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን ጥልቅ ግንኙነት በ”ታይምስ ኦፍ ኢንዲያ” ድረ-ገጽ ላይ በሰፊው ዳሳዋለች።

“ታይምስ ኦፍ ኢንዲያ” በዓለም ላይ በስርጭቱ በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀስና በሕንድ ከፍተኛ ተጽዕኖ ያለው ታላቅ የዜና አውታር ነው።

ራሽሚ አናንድ በጽሑፏ ኢትዮጵያ እና ሕንድ በቅኝ ግዛት ወቅት የነበራቸው ተመሳሳይ ትግል እና የቆየ የንግድ ልውውጥ ዛሬ ለሚታየው ጠንካራ ዲፕሎማሲ መሠረት መሆኑን ገልጻለች።

የኢኮኖሚ አጋርነቸውን በተመለከተ ሕንንድ በኢትዮጵያ ውስጥ ከፍተኛ ኢንቨስትመንት ካላቸው ጥቂት ሀገራት አንዷ መሆኗን ጠቅሰው በተለይም በጨርቃ ጨርቅ፣ በግብርና ማቀነባበሪያ እና በፋርማሲዩቲካል ዘርፍ የሕንድ ኩባንያዎች የኢትዮጵያን የኢንዱስትሪ ልማት እየደገፉ መሆኑን አብራርታለች።

በሌላ በኩል የሕንድ “ዲጂታል ኢንዲያ” ተሞክሮ ለኢትዮጵያ የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ትልቅ ፋይዳ እንዳለውና በሁለቱ ሀገራት የትምህርት ተቋማት መካከል ያለው ትብብር ለሰው ኃይል ልማት ወሳኝ ሚና እየተጫወተ እንደሚኝም ገልጻለች።

በፈረንጆቹ የ2025 የመጨረሻ ወር ላይ የሕንዱ መሪ ናሬንድራ ሞዲ ኢትዮጵያን መጎብኘት ለሁለቱ ሀገራት ግንኙነት ልዩ ዓመት መሆኑን የጠቀሰችው ጸሐፊዋ፣ ኢትዮጵያ በብሪክስ አባልነቷ እና ሕንድ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያላት ተሰሚነት ተደምሮ ለ”ግሎባል ሳውዝ” ድምጽ መሆን እንደሚችሉ አስታውቃለች።

በጄዋሃርላል ኔህሩ ዩኒቨርሲቲ የአፍሪካ ጥናት ማዕከል ረዳት ፕሮፌሰር የሆነችው ራሽሚ ራኒ አናንድ (ዶ/ር) ለስምንት ዓመታት በመምህርነትና በምርምር አገልግላለች። በተለይ በሕንድ-አፍሪካ ግንኙነት፣ በዲፕሎማሲ፣ በልማት እና በጂኦ-ስፓሻል ቴክኖሎጂ ዙሪያ ጥልቅ ዕውቀት ያላት ተመራማሪ እንደሆነች መረጃዎች ያሳያሉ።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review