18ኛ ሳምንት የእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ ዛሬ በሚከናወኑ ሁለት ጨዋታዎች ይጠናቀቃል።
የዘንድሮው ክስተት ቡድን ሰንደርላንድ በስታዲየም ኦፍ ላይት ሊድስ ዩናይትድን ያስተናግዳል። ከስምንት ዓመት በኋላ ወደ ፕሪምየር ሊጉ ያደገው ሰንደርላንድ ካደረጋቸው 17 ጨዋታዎች 27 ነጥብ አግኝቶ 7ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።
በፈረንሳዩ አሰልጣኝ ሬጅ ለ ብሪስ የሚመሩት ጥቋቁር ድመቶቹ በሜዳቸው ምንም ሽንፈት አልገጠማቸውም። ሰሞነኛ ብቃቱ ጥሩ የሆነው ሊድስ ዮናይትድ በ19 ነጥብ 16ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል። እንደ ሰንደርላንድ ሁሉ ከቻምፒየንሺፕ ያደገው ሊድስ ከወራጅ ቀጠናው በስድስት ነጥብ ርቋል።

ጨዋታው 11 ሰዓት ላይ ጅማሮውን ያደርጋል። ክሪስታል ፓላስ ከቶተንሃም ሆትስፐርስ የሚያደርገው የለንደን ደርቢ ፍልሚያ ሌላ የዕለቱ ተጠባቂ ጨዋታ ነው። ጨዋታው በተለይ ለቶተንሃሙ አሰልጣኝ ቶማስ ፍራንክ ወሳኝ ይመስላል።
ዴንማርካዊው የብሬንትፎርድ የቀድሞ አሰልጣኝ ቡድናቸው ወጥ ብቃት ማሳየት አልቻለም። ከዛሬ ጨዋታ በፊት ያከናወኗቸውን ሁለት ተከታታይ ጨዋታ ተሸንፈዋል። በ22 ነጥብ 14ኛ ደረጃ መቀመጡም ደጋፊዎችን አላስደሰተም።
ምሽት 1:30 የሚደረገውን የዛሬ ጨዋታ በሽንፈት ከደመደሙ ቶማስ ፍራንክ በሰሜን ለንደኑ ክለብ የመቆየት እድላቸው ይጠባል። አጀማመሩ ያማረለት ክሪስታል ፓላስ ሰሞነኛ ብቃቱ ጥሩ አይደለም።
በሁሉም ውድድሮች ያደረጓቸውን አራት የመጨረሻ ጨዋታዎች አንድም ያላሸነፈው ክሪስታል ፓላስ በ26 ነጥብ 9ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።
ፓላስ በሜዳው ሰልኸረስት ፓርክ ግን ጠንካራ ቡድን ነው። በውድድር ዓመቱ በማንችስተር ዩናይትድ እና ማንችስተር ሲቲ ብቻ የተሸነፉት።
በሸዋንግዛው ግርማ