ለሰዓታት በሚሊዮኖች ልብ የገባችው አዲስ አበባ

You are currently viewing ለሰዓታት በሚሊዮኖች ልብ የገባችው አዲስ አበባ

AMN- ጥር 7/2018 ዓ.ም

አፍሪካዊቷ መልህቅ አዲስ አበባ የቱሪዝም መሸጋገሪያ ሳትሆን መዳረሻ እንድትሆን ባለፉት በጣት በሚቆጠሩ ዓመታት በተሰሩ ስራዎች የበርካቶች ዓይንና ቀልብ ማረፊያ እየሆነች መጥታለች፡፡

ለዚህ ደግሞ በከተማዋ የተከናወኑ ዓለም ዓቀፍ ጉባኤዎች እና የጉባኤው ተሳታፊዎች የሰጡት ምስክርነት ማረጋገጫ ነው።

የዓለም አቀፉ ታዋቂ የሶሻል ሚዲያ ተጽዕኖ ፈጣሪ አይሾው ስፒድ ከቀናት በፊት ወደ አዲስ አበባ በመምጣቱ፣ በከተማዋ የሚገኙ ታላላቅ የቱሪዝም መዳረሻ ከሆኑት መካከል የአድዋ ድል መታሰቢያ፣ በዓይነቱ ልዩ የሆነውን የአራዳ ፓርክ፣ የሳይንስ ሙዚየም እና በአፍሪካ ትልቁ የሆነውን የመርካቶ የገበያን ጎብኝቷል።

እንዲሁም በግዙፉ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ህንፃ አናት በመውጣት፣ የአዲስ አበባን ገፅታ ለዓለም ያስተዋወቀበት ክስተት ከብዙዎቹ ጥቂቶች መሆናቸውን የአዲስ አበባ ከተማ ቱሪዝም ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ሀንዴ ከበደ ከኤ ኤም ኤን ዲጂታል ጋር ባደረጉት ቆይታ ተናግረዋል።

አይሾው ስፒድ በአዲሰ አበባ በነበረው ቆይታ በዓለም ዙሪያ የሚገኙ የማህበራዊ ሚዲያ ቤተሰቦች ስለ አዲስ አበባ እና ኢትዮጵያ በቂ መረጃ ያገኙበት እንደነበርም አቶ ሁንዴ ገልፀዋል።

አይሾው ስፒድ ባከናወናቸው ተግባራት የአዲስ አበባን ማራኪነት እና የሀገሪቱን የታሪክ ባለቤትነትና ቀደምትነት ለተቀረው ዓለም ለማስተዋወቅ ዓይነተኛ ሚና እንደነበረው ያነሱት አቶ ሁንዴ፣ በዚህም አዲሰ አበባ ለሰዓታት በሚሊዮኖች ልብ እንድትገባ ያደረገ መሆኑን ገልፀዋል።

የቱሪዝም ሀብቶችን ለማስተዋወቅ የተፅዕኖ ፈጣሪዎች ሚና የማይናቅ ነው ያሉት አቶ ሁንዴ ከበደ፣ በከተማዋ እየተከናወኑ ያሉ የቱሪዝም መዳረሻዎችን ለጎብኝዎች መረጃ እንዲያገኙ በማድረግ ረገድ መሰል የማስተዋወቅ ስራዎች ተጠናክረው የሚቀጥሉ መሆናቸውንም ተናግረዋል።

በያለው ጌታነህ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review