ብሬንትፎርድ ከ አርሰናል፡- መድፈኞቹ መሪነታቸውን ለማጠናከር የሚያደርጉት ፍልሚያ

You are currently viewing ብሬንትፎርድ ከ አርሰናል፡- መድፈኞቹ መሪነታቸውን ለማጠናከር የሚያደርጉት ፍልሚያ

AMN የካቲት 05 ቀን 2018 ዓ.ም

የ26ኛ ሳምንት የእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ ዛሬ በሚደረግ አንድ ጨዋታ ይጠናቀቃል፡፡ አርሰናል ወደ ምዕራብ ለንደን አቅንቶ ብሬንትፎርድን ይገጥማል፡፡

በሜዳው ጌትች ኮሚኒቲ ስታዲየም የሚጫወተው ብሬንትፎርድ በርካቶች ከጠበቁት በላይ ውጤታማ እየሆነ ይገኛል፡፡ ክለቡ አሰልጣኙ ቶማስ ፍራንክ ፤ ወሳኝ ተጫዋቾቹን ብሪያን ምቡሞ ፣ ዮዋን ዊሳ እና ክሪስቲያን ኖርጋርድን ሲያጡ ግምቶች ሁሉ ወደ ቻምፒየን ሺፕ ይወርዳል የሚል ነበር፡፡

የቶማስ ፍራንክ የቆሙ ኳሶች ረዳት አሰልጣኝ የነበረው ኪት አንድሪውስ ግን የዋና አሰልጣኝነት ዕድሉን አግኝቶ ተአምር እየሰራ ይገኛል፡፡ ብሬንትፎርድ በሊጉ ካደረጋቸው 25 ጨዋታዎች ከሊቨርፑል እኩል 39 ነጥብ በመሰብሰብ 7ኛ ደረጃን ይዟል፡፡

በመጨረሻ ሁለት የሊግ ጨዋታዎቻቸው አስቶንቪላ እና ኒውካስትል ዩናይትድን ከሜዳቸው ውጪ ገጥመው ያሸነፉት ብሬንትፎርዶች ዛሬም ለአርሰናል ፈተና ይሆናሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡

አርሰናል ከማንችስተር ሲቲ ጋር ያለውን የሦስት ነጥብ ልዩነት ለማስፋት ጨዋታውን የግድ ማሸነፍ አለበት፡፡ ማንችስተር ሲቲ ሊቨርፑል እና ፉልሃምን በተከታታይ ያሸነፈበት መንገድ ለዋንጫ ፉክክሩ ዝግጁ መሆኑን ምልክት የሰጠበት ሆኗል፡፡

ከ22 ዓመታት በኋላ የሊጉ ዋንጫን ከፍ ለማድረግ የተሻለ እድል ያለው አርሰናል በመጨረሻ ሁለት የሊግ ጨዋታዎቹ ሊድስ ዩናይትድ እና ሰንደርላንድን ሰባት ግቦችን አስቆጥሮ አንድም ግባ ሳይቆተርበት መርታት ችሏል፡፡

አርሰናል እና ብሬንትፎርድ ከዚህ ቀደም ባከናወኗቸው ጨዋታዎች አርሰናል የተሻለ ውጤት አለው፡፡ ብሬንትፎርድ ወደ ፕሪምየር ሊግ ባደገበት ዓመት 2021 ላይ አርሰናልን 2ለ0 ካሸነፈ በኋላ ድል ቀንቶት አያውቅም፡፡ ከዚህ ታሪካዊ ጨዋታ በኋላ ስምንት ጨዋታዎችን አድርገው መድፈኞቹ የስድስቱ ባለድል ሲሆኑ ፣ በሁለቱ አቻ ተለያይተዋል፡፡

የዛሬ ተጠባቂ ጨዋታ ምሽት 5 ሰዓት ይጀምራል፡፡

በሸዋምግዛው ግርማ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review