የቃጠሎ አደጋ ሲያጋጥም የሚወሰዱ ጥንቃቄ እርምጃዎች

You are currently viewing የቃጠሎ አደጋ ሲያጋጥም የሚወሰዱ ጥንቃቄ እርምጃዎች
  • Post category:ጤና

AMN -የካቲት 09/2018 ዓ.ም

አብዛኛውን ጊዜ የቃጠሎ አደጋ ሲያጋጥም በድንጋጤ የምንወስዳቸው እርምጃዎች ጉዳቱን ሊያባብሱ ይችላሉ።

የሰውነትን ሙቀት ከማቀዝቀዝ ጀምሮ ተጎጂውን ወደ ሕክምና ተቋም እስከማድረስ ድረስ ሊደረጉ የሚገባቸው ጥንቃቄዎች ምንድን ናቸው?

ዶክተር ቤካ ገቢሳ ከአደጋው መከላከል ጀምሮ ስላለው የሕክምና ሂደት ዝርዝርና በሰውነት ቃጠሎ ወቅት መደረግ ስላለባቸው ተግባራት ለኤ ኤም ኤን አብራርተዋል።

በማህበረሰባችን ውስጥ በከፍተኛ ሁኔታ ከሚከሰቱ አደጋዎች መካከል አንዱ የሆነው የሰውነት ቃጠሎ፣ በማንኛውም የዕድሜ ክልል ላይ የሚገኝን ሰው ሊያጋጥም ይችላል።

አደጋው በሚከሰትበት ወቅት የሚደረጉ ፈጣን እርምጃዎችና ጥንቃቄዎችም የጉዳቱን መጠን ለመቀነስ ብሎም ሕይወትን ለማዳን ወሳኝ ሚና አላቸው።

የቃጠሎ አደጋ በዋናነት የፈላ ፈሳሾች፣ የእሳት አደጋ ፣ የኤሌክትሪክ አደጋ ምክንያቶች ሊከሰት እንደሚችል የቀዶ ሕክምና ስፔሻሊስት የሆኑት ዶክተር ቤካ ገቢሳ ያስረዳሉ፡፡

አደጋው ሲከሰት በፍጥነት መወሰድ ያለባቸው ቀዳሚ እርምጃዎች

👉 ተጎጂውን ከአደጋው አከባቢ መለየት፦ ተጎጂውን ከፈላ ውሃ፣ ከእሳት ወይም ከኤሌክትሪክ ንክኪ በፍጥነት ማራቅ ቀዳሚ ተግባር ነው።

👉 ተቀጣጣይ ነገሮችን ማስወገድ፦ በሰውነት ላይ ያሉ ልብሶችን፣ ጌጣጌጦችንና ሌሎች ለቃጠሎው ሊያባብሱ የሚችሉ ነገሮችን ከሰውነት መለየት

👉 ሰውነትን ማቀዝቀዝ፦ ቃጠሎው የደረሰበትን የሰውነት ክፍል ውሃ በመጠቀም ማቀዝቀዝ ይቻላል። ነገር ግን ከመጠን በላይ ቀዝቃዛ የሆነ ውሃ መጠቀም ለተጨማሪ ጉዳት ስለሚዳርግ ጥንቃቄ ሊደረግበት ይገባል።

👉 መተንፈሻን ማረጋገጥ፦ ተጎጂው በትክክል እየተነፈሰ መሆኑንና የደም ዝውውሩን ሁኔታ መከታተል ለሕይወት አድን ተግባር አስፈላጊ ነው።

ተጎጂው ወደ ጤና ተቋም ከደረሰ በኋላ እንደ ጉዳቱ መጠን ፤የመተንፈስ ችግር ካለ የኦክስጅን ድጋፍ መስጠት፣ በቃጠሎ ምክንያት የሚጠፋን የሰውነት ፈሳሽ መተካትና የህመም ማስታገሻዎችን መስጠት፣ የተቃጠለውን የሰውነት ክፍል በንጹህ የሕክምና ጨርቅ (Gauze) መሸፈን፣ ቁስሉ በኢንፌክሽን እንዳይጠቃ ክትትል ማድረግና ከተጠቃም ተገቢውን ሕክምና መስጠት፣ ለከፍተኛ ቃጠሎ የቆዳ ንቅለ ተከላ (Graft) ቀዶ ጥገና ማድረግ ሕክምናዎች ሊደረጉለት ይችላሉ፡፡

አደጋ ከመከሰቱ በፊት መከላከል ይቀድማል ያሉት ዶክተር ቤካ፣ የፈሉ ፈሳሾችን ከሰዎች አርቆ ማስቀመጥና በተለይም እንደ የሚጥል በሽታ ያሉ የጤና ችግሮች ያሉባቸው ሰዎች ከአደጋ ስፍራዎች እንዲርቁ በማድረግ አደጋውን መቀነስ እንደሚቻል መክረዋል።

በፍሬይሕወት ብርሃኑ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review