AMN- የካቲት 18/2018 ዓ.ም
ግርዛት በኢትዮጵያ ውስጥ ረጅም ዘመናትን ያስቆጠረ ሃይማኖታዊና ባህላዊ መሰረት ያለው ቢሆንም፣ ዘመናዊው ሳይንስ ደግሞ ለጤና ያለውን ከፍተኛ ጠቀሜታ አረጋግጧል።
የህጻናት ስፔሻሊስት ሐኪም የሆኑት ዶክተር ኤርሚያስ ጌታቸው ስለ ግርዛት አስፈላጊነት፣ ስለሚከላከላቸው በሽታዎች እና ወላጆች ሊያደርጓቸው ስለሚገቡ ጥንቃቄዎች ሰፊ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
የወንድ ልጅ ግርዛት አስፈላጊነት
የወንድ ልጅ ግርዛት በህክምናው ዓለም እጅግ አስፈላጊ ከሚባሉ ተግባራት አንዱ ነው።ግርዛት ለምን እንደሚጠቅም ሳይንሳዊ ምክንያቶች መካከል፡-
• የንጽህና አጠባበቅ፦ የብልት ጫፍ ቆዳ ሳይገረዝ በሚቆይበት ጊዜ በቆዳው ስር ቆሻሻዎች የመጠራቀም እድላቸው ሰፊ ሲሆን፣ ይህም ለተለያዩ ኢንፌክሽኖች ያጋልጣል።

• የሽንት ቧንቧ ኢንፌክሽን መከላከል፦ በተለይ ከአንድ ዓመት በታች ያሉ ያልተገረዙ ህጻናት ከተገረዙት አንጻር ከ10 እስከ 15 እጥፍ ለሽንት ቧንቧ ኢንፌክሽን የመጋለጥ እድል አላቸው።
• የአባላዘር በሽታዎችን መቀነስ፦ ግርዛት እንደ ሲፊሊስ፣ ጨብጥ እና የኤች አይ ቪ ቫይረስ ስርጭትን በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚቀንስ በተለያዩ ሀገራት የተደረጉ ጥናቶች ያሳያሉ።
• የካንሰር ስጋትን መቀነስ፦ የተገረዙ ወንዶች በብልት ካንሰር የመያዝ እድላቸው ዝቅተኛ ከመሆኑም በላይ፣ ለትዳር አጋሮቻቸው የማህጸን በር ካንሰር የሚያጋልጡ ቫይረሶችን የመጋራት እድላቸው አነስተኛ ነው።
ግርዛት መቼ እና የት ይከናወን?
ግርዛት በባህላዊም ሆነ በዘመናዊ መንገድ ሊከናወን ቢችልም፣ የህክምና ባለሙያዎች ግን በዘመናዊ የህክምና ተቋማት ውስጥ እንዲደረግ አጥብቀው ይመክራሉ።
ግርዛት በዘመናዊ መልክ መከናወን አለበት፤ ምክንያቱም መሳሪያዎቹ ንጽህናቸው የተጠበቀ ስለሚሆኑ ኢንፌክሽንን ይከላከላሉ፣ ድንገተኛ የደም መፍሰስ ቢከሰትም በአፋጣኝ ለመቆጣጠር ያስችላል።
ግርዛት ከመከናወኑ በፊት ልዩ ጥንቃቄ የሚያስፈልጋቸው ሁኔታዎች፡-

የአፈጣጠር ችግር፦ የሽንት መሽኛ ቀዳዳው ትክክለኛ ቦታ ላይ ካልሆነ ወይም የቆዳው መጠን አነስተኛ ከሆነ።
ያለ ጊዜ መወለድ፦ ህጻኑ ያለ ጊዜው የተወለደ ከሆነ።
የደም መፍሰስ ችግር፦ በቤተሰብ ውስጥ ደም የመርጋት ችግር ለምሳሌ (ሄሞፊሊያ) ካለ፣ ከግርዛት በኋላ ከፍተኛ ደም መፍሰስ እንዳይከሰት ቅድመ ጥንቃቄ ያስፈልጋል።
ግርዛት ቀላል የሚመስል ግን ከፍተኛ ጥንቃቄ የሚሻ ተግባር በመሆኑ፣ ግርዛት ከመከናወኑ በፊት እነዚህ ሁኔታዎች ካሉ የግድ የሀኪም ምክር ማግኘት ያስፈልጋል ሲሉ አጽንዖት ሰጥተዋል።
በተጨማሪም የቆዳው መጠን ሳይበዛም ሆነ ሳይዝል በትክክለኛ ባለሙያ መቆረጥ አለበት ያሉት ዶክተር ኤርሚያስ ጌታቸው፣ ወላጆች ያለምንም ስጋት ልጆቻቸውን በህክምና ተቋም በማስገረዝ ከወደፊት የጤና ችግሮች ሊታደጓቸው እንደሚችሉም አስገንዝበዋል።
በፍሬሕይወት ብርሃኑ