የሚሰማዎት እንቅልፍ እንቅልፍ የሚል ወይስ የድካም ስሜት?

You are currently viewing የሚሰማዎት እንቅልፍ እንቅልፍ የሚል ወይስ የድካም ስሜት?

AMN- የካቲት 26/2018 ዓ.ም

ጥናቶች እንደሚያሳዩት አንዳንድ ሰዎች ምንም ዓይነት የጤና ችግር ሳይኖርባቸዉ የድካም ስሜት ያጋጥማቸዋል፡፡ በሳምንት ዉስጥ ከሁለት እስከ አራት ቀናት ድረስ እንቅልፍ እንቅልፍ የሚል ስሜት የሚኖራቸዉ ሰዎችም አሉ፡፡

በአንዳንድ የዓለም ሀገራት ድካም በታካሚዎች ዘንድ በጣም የተለመደ ቅሬታ ሆኗል፡፡ ሁኔታው በጣም የተለመደ ከመሆኑ የተነሳ የብሔራዊ ጤና አገልግሎት “ሁልጊዜ መድከም” የሚል የራሱ መፈክር አውጥቶለታል።

እንቅልፍ እንቅልፍም ይበል፤ የድካም ስሜት ትርጉሙን እንኳ በትክክል ለማስቀመጥ አስቸጋሪ መሆኑ ነዉ መረጃዎች ሚያሳዩት፡፡ “ድካም (tiredness) ከእንቅልፍ መምጣት (sleepiness) በብዙ መንገድ እንደሚለያዩ ባለሙያዎች ይገልጻሉ፡፡

እንቅልፍ መምጣት ማለት ለመተኛት የመጋለጥ ዝንባሌ መሆኑን የሚናገሩት ባለሙያዎች፣ እንቅልፍና የድካም ስሜት የተሳሰሩ ቢሆኑም ድካም (fatigue) በጣም ዘርፈ-ብዙ ነው፡፡ ድካም፡- የድካም ስሜት መሰማት አጠቃላይ መገለጫ ሲሆን፣ ድካም የሚሰማበት ብዙ መንገዶች አሉ፡፡

ከረጅም የእግር ጉዞ ወይም ከከባድ የስፖርት እንቅስቃሴ በኋላ የሚሰማ የድካም ስሜት አለ፡፡ ይህ ድካም የእውቀት (cognitive) እና የስሜታዊነት ገጽታዎችንም ሊያካትት ይችላል፡፡

ለዚህም ነው በምንደክምበት ጊዜ የሐሳብ መዘበራረቅ የሚገጥመን እና ሥራን እንደ ሸክም የምንቆጥረው ወይም በዙሪያችን ባሉ ሰዎች ላይ የምንቆጣው ይላሉ የዘርፉ አጥኝዎች፡፡ መረጃዎች እንደሚያሳዩት ሳይንቲስቶች በድካም ገጽታዎች ዙሪያ ጠለቅ ያለ ምርምር ማካሄድ የቻሉት ባለፉት አሥር ዓመታት ውስጥ ብቻ ነው፡፡

ይህም የሆነው የአንጎልን ለውጥ በቅጽበት ለማየት የሚያስችሉ የምስል ቴክኖሎጂዎች እና የባዮኬሚካል ምርመራዎች በማደጋቸው እንደሆነ ይገለፃል። “አሁን ስለ ኒውሮባዮሎጂው እና የትኛው የአንጎል ክፍል ድካምን እንደሚረዳ ገና ማወቅ ጀምረናል” ይላሉ ተመራማሪዎቹ፡፡

ሌላው ፈተና ደግሞ ድካም በጣም ግላዊ መሆኑ እና በብዙ ምክንያቶች ሊከሰት መቻሉ ነው። በህመም ምክንያት የሚመጣን እና ከህመም ጋር ግንኙነት የሌለውን ድካም መለየት እጅግ አስፈላጊ መሆኑን ጥናቱ ያሳያል፡፡

የተለያዩ የድካም ዓይነቶችን ለይቶ ማውጣት ከተቻለ፣ በተለየ መንገድ ልናክማቸው እና የበለጠ የተመጣጠነ መፍትሄዎችን ልናቀርብ እንችላለን ይላሉ የዘርፉ ባለሙያዎች፡፡በቂ እንቅልፍ ከማግኘት ጋር በተያያዘም ለአዋቂዎች የሚያስፈልገው መጠን ቢለያይም፣ አብዛኞቹ ሰዎች ሰባት ወይም ከዚያ በላይ ሰዓታት ያስፈልጋቸዋል፡፡

ለረጅም ጊዜ ድካም የሚሰማቸው ሰዎች የመሞት እድላቸው ከሌሎች በበለጠ ከፍተኛ ከመሆኑም በላይ፣ ለጭንቀት እና ለድብርት የመጋለጥ እድላቸው ከፍተኛ መሆኑን ጥናቶችን ጠቅሶ ቢቢሲ አስነብቧል፡፡

በቂ እንቅልፍ ወይም እረፍት ማግኘት አካላዊ ጡንቻዎችን ለመጠገን፣ በሽታ የመከላከል አቅምን ለማሳደግ፣ ስሜቶችን ለመቆጣጠር፣ ትውስታዎችን እና አዳዲስ መረጃዎችን ለማቀናጀት፣ እንዲሁም ሌሎች ወሳኝ ተግባራትን ለማከናወን ያግዛል፡፡

በወንድማገኝ አሰፋ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review