AMN – ጥቅምት 17/2019 ዓ.ም
በትግራይ ክልል የንግድ እንቅስቃሴን የማነቃቃት እና ገበያን የማረጋጋት ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን በክልሉ የፌዴራል መንግስት ባለአደራ አስተዳደር የኢኮኖሚና መልሶ ግንባታ ዋና አስፈጻሚ ቴዎድሮስ አረጋይ (ዶ/ር) ገለጹ።
በክልሉ ሰላም እንዲጸና እና የመልሶ ግንባታ ስራዎች እንዲጠናከሩ የፌዴራል መንግስት በትኩረት እየሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡
በትግራይ ክልል የፌዴራል መንግስት ባለአደራ አስተዳደር የኢኮኖሚና መልሶ ግንባታ ዋና አስፈጻሚ ቴዎድሮስ አረጋይ (ዶ/ር) እንደገለጹት፣ በክልሉ የባለአደራ አስተዳደር ከተቋቋመ ጀምሮ የተጎዱ የማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና የንግድ መዋቅሮችን በመዘርጋት እና ችግሮች በማቃለል ህዝቡ ወደ መደበኛ ህይወቱ ለመመለስ ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ ነው፡፡
በትግራይ ክልል በሕገ-ወጡ የህወሓት ቡድን ምክንያት ተቋርጠው የቆዩ መደበኛ የአገልግሎት ሰጪ ተቋማት እና የመሰረተ ልማት አውታሮች ወደ መደበኛ ስራቸው መመለሳቸውን ዶክተር ቴዎድሮስ ተናግረዋል፡፡
በሕገ ወጡ ሕወሓት የፈረሱ የመንግስት መዋቅሮች መልሶ ለመዘርጋት እና የሕዝብ አገልግሎቶች ለማስቀጠል ጊዜያዊ አስተባባሪዎችን በመመደብ በተጠናከረ ሁኔታ መቀጠሉን ገልጸዋል፡፡
በክልሉ ገበያ እንዲነቃቃ እና የምግብና የምግብ ነክ ሸቀጦች እንዲሟሉ ባለአደራ አስተዳደሩ ከንግዱ ማህበረሰብ ጋር በመተባበር እየሰራ መሆኑን ጠቁመው፣ በዚህም የአቅርቦት እጥረቱ እየተቀረፈ መሆኑን አመልክተዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት የህዝብ የንቅናቄና የውይይት መድረኮች ተጠናክረው መቀጠላቸውን የተናገሩት ዶክተር ቴዎድሮስ፣ ከየመድረኩ የሚነሱ የህብረተሰቡ ፍላጎቶችና ጥያቄዎች መሰረት በማድረግ ለችግሮች ምላሽ እየተሰጠ ነው ብለዋል፡፡
የፍጆታ አቅርቦትን ለማሟላት፣ የንግድ እንቅስቃሴ ለማነቃቃት እና ገበያን ለማረጋጋት ከባለሃብቶች፣ ባንኮች እና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር ውጤታማ ስራዎች መከናወናቸውን ጠቅሰው፣ በአሁኑ ወቅት የምግብ እና የምግብ ነክ ዓይነቶች ወደ ክልሉ እየገቡ መሆኑን አመልክተዋል፡፡
በመቐለ ከተማ አስተዳደር የተጀመረውን የመማር ማስተማር ሂደት በሁሉም አካባቢዎች ለማስጀመር አስፈላጊው ዝግጅት እየተደረገ መሆኑንም ዶክተር ቴዎድሮስ ገልጸዋል፡፡
በትግራይ ክልል ሰላም እንዲጸና እና የመልሶ ግንባታ ስራዎች እንዲጠናከሩ የፌዴራል መንግስት በትኩረት እየሰራ መሆኑን መጠቆማቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡