የመውረድ ስጋት ያለበት ቶተንሃም በክሪስታል ፓላስ ተሸነፈ

You are currently viewing የመውረድ ስጋት ያለበት ቶተንሃም በክሪስታል ፓላስ ተሸነፈ

AMN- የካቲት 27/2018 ዓ.ም

በ29ኛ ሳምንት የእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ የመጨረሻ ጨዋታ ክሪስታል ፓላስ ቶተንሃም ሆትስፐርስን 3ለ1 አሸነፈ።

በቶተንሃም ሆትስፐርስ ሜዳ በተደረገው ጨዋታ ዶሚኒክ ሶላንኬ ባለሜዳውን ቀዳሚ ያደረገች ግብ ቢያስቆጥርም ልዩነት መፍጠር አልቻለም።

ቶተንሃምን በአምበልነት እየመራ ወደ ሜዳ የገባው ተከላካዩ ሚኪ ቫን ደቬን ኢስማኤላ ሳር ላይ የሰራው ጥፋት ፍፁም ቅጣት ምት ከማሰጠቱ በላይ በቀይ ካርድ እንዲወጣ አድርጎታል። የጨዋታው መልክ በዚህ ጥፋት ተቀይሮ ፓላስ 3ለ1 እንዲያሸንፍ ረድቷል።

ለክሪስታል ፓላስ ኢስማኤላ ሳር በፍፁም ቅጣት ምት እና በጨዋታ ሁለት ግቦችን ሲያስቆጥር ፣ ዮርገን ስትራንድ ላርሰን ተጨማሪ ግብ ማስመዝገብ ችሏል።

የመውረድ ስጋቱ እየጠነከረ የመጣበት ቶተንሃም ጊዜያዊ አሰልጣኙ ኢጎር ቱዶርን ከቀጠረ በኋላ ሦስት ተከታታይ ጨዋታ ተሸንፏል።

ባለፉት 11 ጨዋታዎች አንድም ያላሸነፈው የሰሜን ለንደኑ ክለብ ከወራጅ ቀጠናው በአንድ ነጥብ ብቻ ርቆ 16ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።

ቶተንሃም ሆትስፐርስ በቀጣይ የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታው ወደ አንፊልድ አቅንቶ ሊቨርፑልን ይገጥማል። ከዚህ ጨዋታ በፊት በአውሮፓ ቻምፒየንስ ሊግ ከአትሌቲኮ ማድሪድ ጋር ይጫወታል።

በሸዋንግዛው ግርማ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review