AMN መጋቢት 7/2018 ዓ.ም
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር “የሃይማኖት ተቋማት በመደመር መንግስት እይታ” በሚል መሪ ሀሳብ በመዲናዋ ከሚገኙ የተለያዩ የሃይማኖት ተቋማትና አባቶች ጋር ምክክር እያካሄደ ይገኛል፡፡
ከንቲባ አዳነች አቤቤ በመዲናዋ ከሚገኙ የእስልምና እምነት አባቶች ጋር የማጠቃለያ ምክክር ያካሄዱ ሲሆን ከተሳታፊዎች ለተነሱ ጥያቄዎች እና አስተያየቶች ምላሽ እና ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
የሙስሊሙ ህዝብ በሃገረ መንግስት ግንባታ ዉስጥ የማይተካ አስተዋጽኦ ማበርከቱን ያነሱት ከንቲባ አዳነች አቤቤ ከታሪክ ፤ ቅርሶችን ከመጠበቅ፤ የሃገር ሉአላዊነትን ከማስከበር ፤ ከልማትና ከትዉልድ ግንበታ አንጻር የጎላ ሚና እንዳለዉ ገልጸዋል፡፡
የሙስሊሙ ማህበረሰብ በማህበራዊ ፤ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ዘርፎች ላይ በመሳተፍ ጭምር ለሃገረ መንግስት ግንባታ የላቀ አስተዋጽኦ በማበርከት ላይ ይገኛል፡፡
ኢትዮጵያ ከእስልምና አንጻር የምትታወቅባቸዉ በርካታ ቅርሶች ፤ ታሪኮች፤ ትዉፊቶች አላት፤ እነዚህ ትዉፊቶች በህዝበ ሙስሊሙ ተጠብቀዉ እንዲቆዩ ተደርጓል፤ ኢትዮጵያንም አስተዋዉቀዋል ብለዋል፡፡

የመደመር መንግስት የተናጠል ሳይሆን የተደመረ አካሄድ እና አቅም ለሃገረ መንግስት ግንባታ ትልቅ ድርሻ አለዉ ብሎ ያምናል ያሉት ከንቲባ አዳነች አቤቤ ሃገራዊ እሴቶችን ማጠናከር እና ዉስንነቶችን በጋራ መቅረፍ እንደሚገባም አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
ኢትዮጵያ በብዝሃነት የምትታወቅ ሃገር ከመሆኗ አንጻር በብልጽግና መርህ መሰረት መንግስታዊ ሃይማኖትም ሆነ ሃይማኖታዊ መንግስት እንደሌለ ነዉ ያረጋገጡት፡፡
መንግስት ሁሉንም ሃይማኖቶች እኩል ይመለከታል፤ አንዱን አቅርቦ ሌላዉን አርቆ የሚያይበት አካሄድ የለም ብለዋል፡፡
ሃገረ መንግስቱ ተገንብቶ እንዳይጠናከር ተግዳሮት የሆነዉ ይህ አካሄድ ስለሆነ ይህ እሳቤ መቀጠል የለበትም፤ ለሁሉም ሃይማኖቶች እኩል የምትበቃ ሃገር በጋራ ልንገነባ ይገባል ሲሉ ገልጸዋል፡፡
ከአመራርነት አንጻርም እያንዳንዱ አመራር የግል ሃይማኖት ሊኖረዉ ይችላል ሲያገለግል ግን የሁሉም አገልጋይ ሆኖ ነዉ፤ የተለየ አሰራር የለም፤ ሃይማኖታዊ እሴቶችን አክብረን በፍትሃሚነት እና እኩልነት ህዝባችንን እናገለግላለን ብለዋል፡፡
የሙስሊሙ ህዝብ እንደ ትላንትናዉ ሁሉ ዛሬም በሃገረ መንግስት ግንባታ ሂደት ዉስጥ የበኩሉን ደርሻ አጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል፡፡
በወንድማገኝ አሰፋ