AMN – ሚያዝያ 15/2018 ዓ.ም
በአሁኑ ወቅት የሰው ሰራሽ አስተውሎት በዓለም አቀፍ ደረጃ የሕክምና አገልግሎት አሰጣጥን ከመሠረቱ እየቀየረ ይገኛል። ኢትዮጵያም ይህንን የቴክኖሎጂ ሽግግር ወደ ጤናው ዘርፍ በማስገባት፣ የሕክምና ጥራትን ለማሻሻልና ተደራሽነትን ለማስፋት ከፍተኛ ጥረት እያደረገች ትገኛለች፡፡
በተለይም ውስብስብ የሆኑ የሕክምና ምስሎችን በመተንተን፣ በሽታዎችን ቀድሞ በመለየት እና የጤና መረጃ አያያዝን በማዘመን ረገድ ቴክኖሎጂው እንደ ዋነኛ መፍትሄ እየታየ ነው።
ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት የሰው ሰራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጂን በጤናው ዘርፍ ለማላመድ እና አገልግሎቱን ለማቀላጠፍ በርካታ ተስፋ ሰጪ እርምጃዎችን እየወሰደች ትገኛለች።
በኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት እና በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር አማካኝነት እየተሰሩ ያሉ ስራዎች ለዚህ ተጠቃሽ ናቸው።

የሰው ሰራሽ አስተውሎት በኢትዮጵያ በጤናው ዘርፍ የህክምና ምስል ትንተና ውጤቶችን በቀላሉና በአጠረ ጊዜ ለመለየት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያደረገ ይገኛል፡፡
በተለይም የራጅ እና የሲቲ ስካን ምስሎችን በሰው ሰራሽ አስተውሎት በማንበብ በሽታን በፍጥነት ለመለየት እየተቻለ መሆኑ ቴክኖሎጂው በጤናው ዘርፍ እያበረከተ ያለውን አስተዋጽኦ ያሳል፡፡
የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩትም ከሳንባ ነቀርሳ እና ከጡት ካንሰር ጋር የተያያዙ የራጅ ምስሎችን በመተንተን በሽታውን የሚለ የሰው ሰራሽ አስተውሎት ሶፍትዌር አበልፅጓል።
ይህ ቴክኖሎጂ በጤና ጣቢያዎች ያለ የሰው ኃይል እጥረት ምርመራው እንዳይዘገይ ትልቅ እገዛ እያደረገ እንደሚገኝ መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡
ሌላው የጤና መረጃ አያያዝ እና ዲጂታይዜሽን በተመለከተም የታካሚዎችን መረጃ በወረቀት ከመያዝ ይልቅ በዲጂታል መንገድ በማቀናጀት ለትንተና ዝግጁ የማድረግ ስራ እየተሰራ ነው።
ለዚህም የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ከኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር እና ከኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩቱ ጋር በመተባበር የዲጂታል ጤና ስትራቴጂን እየተገበረ ይገኛል፡፡

ይህም የታካሚዎችን ታሪክ መሠረት በማድረግ ለወደፊት ሊከሰቱ የሚችሉ ወረርሽኞችን ቀድሞ ለመተንበይ የሚያስችል መሠረት እየጣለ ነው።
በተጨማሪም የላቦራቶሪ ምርመራዎችን ማዘመንን በተመለከተም በአጉሊ መነጽር የሚታዩ ጥገኛ ተህዋስያንን በሰው ሰራሽ አስተውሎት አማካኝነት የመለየት ስራ ተጀምሯል።
ለአብነትም የወባ በሽታን ለመለየት የሚያስችል የሰው ሰራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጂ በሙከራ ደረጃ ላይ ይገኛል። ይህ ቴክኖሎጂ የደም ናሙና ስላይዶችን በከፍተኛ ፍጥነት በማንበብ የጥገኛ ተህዋስያኑን አይነት እና መጠን መለየት ይችላል።
በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ወቅትም የሰው ሰራሽ አስተውሎት ለክትትል እና ለግንዛቤ ስራዎች ከፍተኛ ድርሻ ነበረው። በወቅቱ የነበሩ አውቶማቲክ የመልዕክት ምላሽ ሰጪዎች ስለ በሽታው መረጃ በመስጠት እና ምልክቶችን በመለየት ረገድ ጥቅም ላይ ውለዋል። በተጨማሪም የቫይረሱን ስርጭት ለመተንበይ የሚረዱ የሰው ሰራሽ አስተውሎት ሞዴሎች ስራ ላይ ውለው ነበር።
በአጠቃላይ ኢትዮጵያ የሰው ሰራሽ አስተውሎትን በጤናው ዘርፍ ለመጠቀም ያላትን ቁርጠኝነት ለማሳየት የሰው ሰራሽ አስተውሎት ፖሊሲ ቀርጻ እየተንቀሳቀሰች ሲሆን፣ በተለይም በምርመራ ረገድ የኢንስቲትዩቱ ውጤቶች ተጨባጭ ማስረጃዎች መሆናቸውን ከጤና ሚኒስቴር፣ ከኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት እና ከሌሎች ዓለም አቀፍ የቴክኖሎጂ እና የጤና ሪፖርቶች ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
በአስማረ መኮንን