AMN ሚያዝያ 25/2018
የኢትዮጵያ አምራቾች ከማምረት ባለፈ የአፍሪካን ገበያ መጠቀም የሚያስችል የንግድ ትስስር መፍጠር እንዳለባቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አስገነዘቡ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከሚያዝያ 25 እስከ 30 ቀን 2018 ዓ.ም የሚቆየውን የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ኤክስፖ መርቀው ከፍተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በዚህ ወቅት እንደተናገሩት፤ ባለፉት አራት ዓመታት በውጭ ምንዛሬ ከውጭ ይገቡ የነበሩ ምርቶችን በሀገር ውስጥ በማምረት ረገድ ከፍተኛ ስኬት ተመዝግቧል።

አምራቾችና የኢንዱስትሪ ዘርፍ ተዋንያን የኢኮኖሚ አርበኝነትን ሊላበሱ እንደሚገባ የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በዚህም ሌብነትና ኮንትሮባንድን በመጸየፍ እውነተኛ የኢኮኖሚ አርበኛ መሆን ያስፈልጋል ብለዋል።
የኢትዮጵያ አምራቾች በአገር ውስጥ የማምረት ተግባር ላይ ብቻ ተወስነው የሚቆዩበት ጊዜ አብቅቶ፣ አሁን ወደ አፍሪካ ሰፊ ገበያ የሚገቡበት ወቅት ላይ መሆኑንም ነው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) የገለጹት።
እስካሁን “አምርቱ” በሚል ማበረታቻ ሲደረግ የነበረው ጥረት አሁን አምራቾች የአህጉሪቱን የንግድ ዕድሎች ለመቀላቀል እንዲወጡና እንዲሰማሩ ጥሪ አስተላልፈዋል።
አምራቾች አቅም ካላቸው በግል፣ ካልሆነም በጋራ በመጣመር አሊያም ከመንግሥት ጋር በመቀናጀት ኩባንያዎችን በመመስረት ወደ አፍሪካ አገራት ዘልቆ መግባት አገራዊ ግዴታቸው ሊሆን እንደሚገባም አመልክተዋል።

ኢትዮጵያ በራሷ ትልቅ ገበያ ያላት አገር መሆኗን ያስታወሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በአፍሪካ ደረጃ ያለውን ሰፊ የንግድ ዕድል ለመጠቀም አምራቾች ከማምረት ባለፈ ገበያውን ለመቆጣጠር መዘጋጀት እንዳለባቸው ተናግረዋል።
አንዱ አምራች እዚህ እያመረተ ሌላው ደግሞ በውጭ አገራት እያከፋፈለ የአፍሪካን የንግድ ሰንሰለት መቆጣጠር ለነገ የማይባል የቤት ሥራ መሆኑን ጠቅሰው፤ ይህ ትልቅ ራዕይ ከግብ እንዲደርስም መንግሥት ለዘርፉ ምቹ ሁኔታዎችን ለመፍጠርና አስፈላጊ የሆኑ ድጋፎችን ለማድረግ የራሱን የቤት ሥራ በአግባቡ እንደሚወጣ አረጋግጠዋል።