AMN – መጋቢት 14/2018 ዓ.ም
በአፍሪካ እንደሚገኙ አገራት ሁሉ በኢትዮጵያም ተላላፊ በሽታዎች በስፋት እንደሚስተዋሉ የሕጻናት ስፔሻሊስት ሐኪም ዶክተር ዓብይ አያሌው ገልጸዋል።
ሐኪሙ በተለይ ከመተንፈሻ አካል ጋር የተያያዙ ሕመሞች በቀጥታና በተዘዋዋሪ መንገዶች እንዴት ሊሰራጩ እንደሚችሉ ለኤ ኤም ኤን ዝርዝር ማብራሪያ ሰጥተዋል። እንደ ዶክተር አቢይ ገለጻ፣ በሽታዎች በሁለት ዋና ዋና መንገዶች ይተላለፋሉ።
አንደኛው፤ በቀጥተኛ መንገድ ሲሆን ይህም ፣ የታመመ ሰው እጁን በአግባቡ ካልታጠበ በንክኪ፣በመጨባበጥ በሽታን ሊያስተላልፍ ይችላል።

እንደ ጉንፋንና የሳምባ ምች ያሉ ሕመሞች ከአፍንጫ በሚወጣ ፈሳሽ አማካኝነት ይሰራጫሉ። የታመመው ሰው ፊቱን ወይም አፍንጫውን ነክቶ ሌላ ሰውን ሲጨብጥ፣ ያም ሰው ፊቱንና አይኑን ሲነካ በሽታው በቀጥታ ይተላለፋል።
ሳል ያለበት ሰው በሚስልበት ጊዜ በአይን የሚታዩና የማይታዩ ብናኞች እስከ ሁለት ሜትር ርቀት በመፈናጠር ወደ ሌላ ሰው አፍና አፍንጫ በመግባት በሽታን ያመጣሉ።
ሁለተኛው በተዘዋዋሪ መንገድ በአየር ወለድ የሚተላለፍ ነው፡፡ አንዳንድ ጀርሞች በአየር ላይ ለረጅም ጊዜ የመቆየት ባህሪ አላቸው። በዚህም የታመመ ሰው በሌለበት አካባቢ እንኳን አየሩን በመተንፈስ ብቻ በሽታ ሊይዝ ይችላል። ይህም በጋራ የምንጠቀማቸው ጠረጴዛዎች፣ ወንበሮች፣ ሳህኖችና ማንኪያዎች በሽታን ሊያስተላልፉ ይችላሉ።
እንደ ትንኝና ዝንብ ያሉ ነፍሳት በሽታን ከአንድ ሰው ወደ ሌላው በማስተላለፍ ረገድ ከፍተኛ ድርሻ አላቸው። ለምሳሌ ወባ በትንኝ አማካኝነት የሚተላለፍ በሽታ ሲሆን፣ ዝንብ ደግሞ በቆሸሸ ቦታ አርፋ ጀርሞችን ወደ ምግብና መጠጥ በማምጣት በሽታን ታሰራጫለች።

መፍትሔው
በሽታዎች የሚተላለፉባቸውን መንገዶች ማወቅ የመከላከያ ስልቶችን ለመቀየስ እንደሚረዳ የገለጹት ዶክተር ዓብይ፣ የግልና የአካባቢ ንጽህና መጠበቅ ፤ ማለትም እጅን በሳሙናና በውሃ መታጠብ እንዲሁም የአካባቢን ንጽህና መጠበቅ ቀዳሚው ተግባር ነው።
እንደ ሕጻናት ማቆያና ትምህርት ቤቶች ያሉ ሰዎች የሚበዙባቸው አካባቢዎች ለመጸዳጃና ለመታጠቢያ ክፍሎች ልዩ ትኩረት መስጠት አለባቸው። በተለይ በሕጻናት ማቆያ አካባቢዎች የሚታይ መጠነኛ መዘናጋት በሽታው በከፍተኛ ፍጥነት እንዲሰራጭ ስለሚያደርግ ጥንቃቄ ሊደረግ ይገባል ሲሉ ዶክተሩ በአጽኖት አሳስበዋል።
በፍሬሕይወት ብርሃኑ