የመካከለኛው ምስራቅ ወቅታዊ ቀውስ እና በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ላይ ያለው ተፅዕኖ

You are currently viewing የመካከለኛው ምስራቅ ወቅታዊ ቀውስ እና በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ላይ ያለው ተፅዕኖ

AMN-መጋቢት 17/2018 ዓ.ም

በመካከለኛው ምስራቅ እየተባባሰ የመጣው ወቅታዊ ግጭት በአለም አቀፍ ኢኮኖሚ ላይ እያሳደረ ያለው ጫና በተለይም እንደ ኢትዮጵያ ባሉ በማደግ ላይ ባሉ ሀገራት ላይ የራሱን ጥላ ማሳረፉ ይታወቃል።

የምጣኔ ሀብት ባለሙያው አቶ ዮሐንስ በቀለ ለአዲስ ሚዲያ ኔትወርክ እንደገለጹት፤ ግጭቱ በተለይ በገልፍ ሀገራት አካባቢ መስፋፋቱ ከኢነርጂ፣ከንግድ መስመሮች መቆራረጥ እና ከአቪዬሽን ዘርፍ ጋር ተያይዞ ቀጥተኛ የሆነ የኢኮኖሚ መስተጓጎል እየፈጠረ እንደሚገኝ ባለሙያው አንስተዋል።

እንደ ባለሙያው ገለፃ የሆርሙዝ ወሽመጥ መዘጋት እና የንግድ መርከቦች እንቅስቃሴ መስተጓጎል በአለም አቀፍ ደረጃ የገቢ እና ወጪ ንግድ ላይ ከፍተኛ ጫና ማሳደሩን ቀጥሏል ብለዋል።

ኢትዮጵያ መቶ በመቶ ነዳጅን ከውጭ የምታስገባ ሀገር በመሆኗ በዚህ ቀውስ ምክንያት የሚፈጠረው የዋጋ ንረት በሀገር ውስጥ ትራንስፖርት እና በምግብ ምርቶች ዋጋ ላይ ቀጥተኛ ተፅዕኖም ይኖረዋል ሲሉ ምልከታቸውን አስረድተዋል።

ከነዳጅ በተጨማሪም ለግብርና ምርታማነት ወሳኝ የሆኑ እንደ ማዳበሪያ ያሉ ግብዓቶች ከውጭ የሚገቡ በመሆናቸው፤ የቀውሱ መባባስ በምግብ ዋጋ ንረት ላይ የሚፈጥረው ጫና የዜጎችን የኑሮ ውድነት ሊያባብሰው እንደሚችል ተመልክቷል።

በተለይም የነዳጅ ማምረቻ ፋብሪካዎች ወደ ቀድሞ የምርት አቅማቸው ለመመለስ ዓመታት ሊፈጅባቸው እንደሚችል የሚጠቁሙ ሪፖርቶች መኖራቸው ችግሩ ለአጭር ጊዜ ብቻ የሚቆይ አለመሆኑን አስገንዝበዋል።

መንግስት ይህንን ከውጭ የሚመጣ የኢኮኖሚ ጫና ለመቋቋም የተለያዩ የመፍትሄ አቅጣጫዎችን ተግባራዊ እያደረገ ይገኛል።

ከነዚህም መካከል የውጭ ምንዛሬ ክምችትን ለመጠበቅ ሲባል የቅንጦት ዕቃዎችን ወደ ሀገር ውስጥ ማስገባት መቀነስ አልፎም ማቆም አንዱ አማራጭ ሊሆን እንደሚገባ ምክረ ሀሳባቸውን አጋርተዋል።

በተጨማሪም ነዳጅን ያለ ብክነት በቁጠባ መጠቀም፣ ቅድሚያ ለሚሰጣቸው ወሳኝ ተግባራት ብቻ ማዋል እንዲሁም እንደ ኤሌክትሪክ ባቡር ያሉ የህዝብ ትራንስፖርት አማራጮችን በስፋት መጠቀም የተፅዕኖ ደረጃውን ለመቀነስ እንደሚረዱ ባለሙያው አመላክተዋል።

የምጣኔ ሀብት ባለሙያው አቶ ዮሐንስ ከኤ ኤም ኤን ጋር በነበራቸው ቆይታም፣በግብርናው ዘርፍ ከውጭ የሚገባውን ማዳበሪያ ለመተካት የተፈጥሮ ማዳበሪያዎችን በስፋት ማምረትና መጠቀም ለምግብ ዋጋ መረጋጋት ወሳኝ መሆኑንም አመላክተዋል ።

በሚካኤል ህሩይ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review