የዋሊያዎቹ ተጠባቂ ፍልሚያዎች

You are currently viewing የዋሊያዎቹ ተጠባቂ ፍልሚያዎች

ኢትዮጵያና የአፍሪካ ዋንጫ ታሪክ ጥልቅ ቁርኝት አላቸው፤ እ.ኤ.አ በ1957 አህጉራዊው የእግር ኳስ ማህበር ሲመሰረትም ሆነ የመጀመሪያው ፉክክር ሲጀመር፣ የኢትዮጵያ ስም በቀዳሚነት የሚጠቀስ ነበር። በ1962 የድል አክሊል በመድፋት የአህጉሪቱ የእግር ኳስ ንግሥት የነበረችው ኢትዮጵያ፣ ባለፉት አሥርተ ዓመታት ግን በታሪኳ የማይመጥን ረጅም የውጤት ማጣት ውስጥ ቆይታለች።

በደቡብ አፍሪካውና በካሜሩኑ የአፍሪካ ዋንጫዎች ላይ ብቅ ብሎ የነበረው ተስፋም ብዙም ሳይዘልቅ ተዳፍኗል። በተለይም ደቡብ አፍሪካ ባዘጋጀችው የ2013ቱ የአፍሪካ ዋንጫ፣ ዋሊያዎቹ ከ31 ዓመታት በኋላ ወደ አህጉራዊው መድረክ ሲመለሱ ያሳዩት ወጥ የሆነ የኳስ ቁጥጥርና ማራኪ የጨዋታ ስልት በመላው አፍሪካ አድናቆትን አትርፎ ነበር። በተለይም በወቅቱ ሻምፒዮን ከነበረችው ናይጄሪያ ጋር እስከ መጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ድረስ የነበረው ብርቱ ፉክክርና ከዛምቢያ ጋር የአቻ ውጤት የተጠናቀቀው ጨዋታ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ጭላንጭል ተስፋ ያሳየ አጋጣሚ ሆኖ ተመዝግቧል።

በተመሳሳይ በ2021 የካሜሩን ቆይታ ምንም እንኳን ቡድኑ ከምድቡ ማለፍ ባይችልም፣ ወጣትና ተስፋ ሰጪ ተጫዋቾችን ይዞ በታላላቅ ኮከቦች ፊት ያሳየው ድፍረት የተሞላበት እንቅስቃሴ ለወደፊቱ ትልቅ ትምህርት ጥሎ አልፏል። እነዚህ ሁለት ተሳትፎዎች ኢትዮጵያ በሜዳ ላይ ያሳየችው የቴክኒክ ብቃትና የተጫዋቾቿ መናበብ፣ በትክክለኛ ዝግጅትና በስነ-ልቦና ጥንካሬ የታጀበ ከሆነ አሁንም ከአህጉሪቱ ውጤታማ ብሔራዊ ቡድኖች መካከል መሰለፍ እንደምትችል ትልቅ ማሳያ ናቸው።

አሁን ዳግም በምስራቅ አፍሪካ በሚስተናገደው የ2027 አፍሪካ ዋንጫ ውድድር ላይ ደምቆ ለመታየት አዲስ የዝግጅት ምዕራፍ ከፍቷል። በኬንያ፣ ዩጋንዳ እና ታንዛኒያ በጋራ አዘጋጅነት ለሚካሄደው ይህ የአፍሪካ ዋንጫ ቅድመ ማጣሪያ ጉዞ ተጀምሯል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን (ዋሊያዎቹ) በዚህ የመጀመሪያ ምዕራፍ ከደሴቲቱ ሀገር ሳኦ ቶሜ እና ፕሪንሲፔ ጋር እንዲገናኙ ተደልድለዋል። ይህ የሁለት ግጥሚያዎች ፍልሚያ ዋሊያዎቹን ወደ ዋናው የምድብ ማጣሪያ ለማሸጋገር ወሳኝ ሲሆን፣ የመጀመሪያውን ጨዋታ በትናንትናው ዕለት ያካሄደ ሲሆን፣ የመልሱ ጨዋታ ደግሞ በቅርቡ ካፍ ባጸደቀውና በታደሰው የድሬዳዋ ስታዲየም መጋቢት 22 ቀን 2018 ዓ.ም እንደሚካሄድ ይጠበቃል።

ኢትዮጵያ በ2027 የአፍሪካ ዋንጫ (AFCON) ቅድመ ማጣሪያ ላይ ከሳኦ ቶሜ እና ፕሪንሲፔ ጋር መደልደሏ ወደ ዋናው የምድብ ማጣሪያ ለማለፍ ወርቃማ ዕድል እንዳላት ማሳያ ተደርጎ ይወሰዳል። ሳኦ ቶሜ እና ፕሪንሲፔ በአፍሪካ እግር ኳስ ውስጥ አዳጊ ከሚባሉ ሀገራት ተርታ ትመደባለች። እስከ ዛሬ ድረስ በአፍሪካ ዋንጫ የመጨረሻው ውድድር ላይ አንድም ጊዜ ተሳትፋ አታውቅም። የካፍ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት ሳኦ ቶሜ እና ፕሪንሲፔ በፊፋ የደረጃ ሰንጠረዥ 188ኛ ደረጃ ላይ የምትገኝ ሲሆን፣ ዋሊያዎቹ ደግሞ በ145ኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ።

ይህ የ43 ደረጃዎች ልዩነት ለኢትዮጵያ አንጻራዊ ብልጫን የሚሰጥ ሲሆን፣ ሳኦ ቶሜ ባለፉት 10 ዓመታት ካደረገቻቸው የማጣሪያ ጨዋታዎች ውስጥ ከ80 በመቶ በላይ የሚሆኑትን በሽንፈት አጠናቃለች፡፡ እንደዚሁም በ2023 ማጣሪያ ላይ ብቻ 22 ጎሎች የተቆጠሩባት መሆኑ፣ ለኢትዮጵያ አጥቂዎች ሰፊ የጎል ዕድል እንደሚኖር ማሳያ ነው። በ2023 ማጣሪያ ላይ በናይጄሪያ 10 ለ 0 በሆነ ሰፊ ውጤት መሸነፏ የሚታወስ ሲሆን፣ ይህም በመከላከያ መስመር ላይ ያለባትን ከፍተኛ ድክመት ያሳያል። ሆኖም ኢትዮጵያ ባለፉት አምስት ዓለም አቀፍ ጨዋታዎች ያስመዘገበችው ዝቅተኛ የጎል አማካይ (በጨዋታ 0 ነጥብ 8 ጎል)፣ በአሰልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ ስር የሚገኘው ስብስብ በአጥቂ መስመሩ ላይ ከፍተኛ ጥንቃቄና ስራ እንደሚጠይቀው መረጃዎች ይጠቁማሉ።

የመጀመሪያው ጨዋታ በሞሮኮ መደረጉ ለኢትዮጵያ እንደ ገለልተኛ ሜዳ የሚቆጠር ሲሆን፣ የመልሱ ጨዋታ በድሬዳዋ ስታዲየም መደረጉ ቡድኑን በከፍተኛ ስነ-ልቦና እንዲገፋ ያደርገዋል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከዓመታት ስደት በኋላ በገዛ ሜዳው የመጫወት ዕድል ማግኘቱ፣ ከስፖርታዊ ድል ባለፈ ትልቅ ስነ-ልቦናዊና ሀገራዊ ፋይዳ አለው። በሌላም በኩል ሳኦ ቶሜን የመሰሉ ከባህር ጠለል በላይ ዝቅ ባለ ስፍራ የሚገኙ ሀገራት፣ በኢትዮጵያ ያለውን የከፍታና የአየር ጸባይ ተቋቁሞ መጫወት ፈታኝ ይሆንባቸዋል። ይህም ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ተፈጥሯዊ የሜዳ ላይ ብልጫን ይሰጣል።

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን መረጃዎች እንደሚጠቁሙት፣ ብሔራዊ ቡድኑ በሜዳው ወቅት ያለው የማሸነፍ ዕድል ከሜዳ ውጭ ካለው ጨዋታ በ65 በመቶ ብልጫ አለው። ይህ በሜዳ የመጫወት ዕድል፣ ለተጫዋቾች የሚሰጠው ስነ-ልቦናዊ መረጋጋትና ከጉዞ ድካም ነፃ መሆን፣ ለ2027ቱ የአፍሪካ ዋንጫ የሚደረገውን ጉዞ በስኬት ለመጀመር ወሳኝ ግብዓት ነው። በድሬዳዋ የሚደረገው የመልስ ጨዋታ፣ ዋሊያዎቹ ወደ ዋናው የምድብ ድልድል (48 ሀገራት ወደሚሳተፉበት) ለመሸጋገር ያላቸውን የላቀ ግምት ወደ እውነታ የሚቀይሩበት መድረክ እንደሚሆን ይጠበቃል።

በአሰልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ የሚመራው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ለዚህ ውድድር ትልቅ ተስፋ ሰንቆ ነው ወደ ውድድር ያቀናው። አሰልጣኙ ልምድ ያላቸውንና በሀገር ውስጥ ሊግ ብቃታቸውን ያሳዩ 23 ተጫዋቾችን ያካተተ ስብስብ የያዙ ሲሆን፣ ቡድኑ ካለፉት ሁለት የአፍሪካ ዋንጫዎች መቅረቱን ተከትሎ አሁን ዳግም ወደ አህጉራዊ መድረክ ለመመለስ ከፍተኛ መነሳሳት ላይ ነው። ከዚህ ቀደም ዋሊያዎቹ በ2018 የዓለም ዋንጫ ቅድመ ማጣሪያ ላይ ሳኦ ቶሜን በድምር ውጤት 3 ለ 1 አሸንፈው ማለፋቸው የሚታወስ ሲሆን፣ አሁንም ያንን ድል በመድገም ወደ ዋናው የምድብ ድልድል ለመቀላቀል ሰፊ ዕድል አላቸው ተብሎ ይታመናል። ይህ ጉዞ ዋሊያዎቹ ለአህጉራዊ ክብር ያላቸውን ናፍቆት የሚወጡበት የመጀመሪያው ወሳኝ ምዕራፍ ነው።

እንደ የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን እና የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን መረጃዎች መሠረት፣ ኢትዮጵያ በዚህ ደረጃ ማለፍ ካቃታት ወደ ዋናው የምድብ ድልድል (48 ሀገራት ወደሚሳተፉበት) መግባት አትችልም። የ2027 የአፍሪካ ዋንጫ (AFCON) የቅድመ ማጣሪያ ጨዋታዎች፣ በአህጉሪቱ ዝቅተኛ የፊፋ ደረጃ ያላቸው ስምንት ብሔራዊ ቡድኖች ወደ ዋናው የምድብ ድልድል ለመግባት የሚያደርጉት የ‘ሞት ሽረት’ ፍልሚያ ነው። እነዚህ ጨዋታዎች በሜዳና ከሜዳ ውጭ በሚደረጉ የደርሶ መልስ ውጤቶች የሚወሰኑ ሲሆን፣ አራት አሸናፊ ቡድኖች ብቻ ናቸው ቀሪዎቹን 44 ከፍተኛ ደረጃ ያላቸው ሀገራት ተቀላቅለው በ12 ምድቦች ውስጥ የሚደለደሉት።

ከ2012 በፊት የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያዎች ሁሉንም ሀገራት በቀጥታ በምድብ በመከፋፈል ይካሄዱ ነበር። ነገር ግን የተሳታፊ ሀገራት ቁጥር እየጨመረ በመምጣቱና የጨዋታዎችን ጥራት ለመጠበቅ ሲባል፣ በፊፋ ደረጃቸው ዝቅተኛ የሆኑ ሀገራት እርስ በእርስ ተጫውተው እንዲያልፉ የሚያደርግ የቅድመ ማጣሪያ ስርዓት በካፍ ተዘረጋ። በተለይ እ.ኤ.አ ከ2019 የግብፅ የአፍሪካ ዋንጫ ጀምሮ የተሳታፊ ሀገራት ቁጥር ከ16 ወደ 24 ከፍ ማለቱን ተከትሎ፣ የማጣሪያው ሂደት ይበልጥ ስልታዊ እንዲሆን ተደርጎ ዝቅተኛ ደረጃ ያላቸውን 8 ሀገራት በማጣመር በቅድመ ማጣሪያው እንዲሳተፉና አሸናፊዎቹ ሀገራትም ወደ ዋናው የምድብ ድልድል እንዲቀላቀሉ ይደረጋል፡፡

ኢትዮጵያና ሳኦ ቶሜ እና ፕሪንሲፔ ከሚያደርጉት ውድድር በተጨማሪ ኤርትራ ከላይቤሪያ፣ ደቡብ ሱዳን ከሞሪሽየስ እንደዚሁም ቻድ ከሞሪታኒያ የቅድመ ማጣሪ ውድድሮችን የሚያከናውኑ ሀገራት ናቸው፡፡ አሸናፊዎቹ ቡድኖች በቀጥታ ወደ 48ቱ ሀገራት የምድብ ድልድል ውስጥ በመግባት፣ ቢያንስ ስድስት ዓለም አቀፍ ጨዋታዎችን የማድረግና ከታላላቅ የአፍሪካ ኮከቦች ጋር የመጋጠም ዕድል ያገኛሉ፡፡ በሰኔ ወር 2018 ዓ.ም ከሚጀመረው ዋናው የምድብ ማጣሪያ ይቀላቀላሉ።

በሳህሉ ብርሃኑ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review