AMN – መጋቢት 21/2018 ዓ.ም
የጥርስ ሕክምና ጤናን ከመጠበቅ ባለፈ ለሰው ልጅ ውበትና በራስ መተማመን ያለው ፋይዳ ከፍተኛ መሆኑ ይነገራል። በተለይም የሆሊውድ ስማይል የሕክምና ዓይነት በዘመናዊው ዓለም በከፍተኛ ደረጃ ተመራጭ እየሆነ መጥቷል።
የጥርስ ሕክምና የጤና እክል ሲያጋጥም እና ውበትን ማዕከል አድርጎ የሚከናወን የሕክምና አይነት መሆኑን የጥርስ ሀኪም የሆኑት ዶክተር ሳውዳ ሲራጅ ከኤ ኤም ኤን ጋር በነበራቸው ቆይታ አብራርተዋል።
ሆሊውድ ስማይል ሰዎች ጥርሳቸው ማራኪ፣ ነጭና ቀጥ ያለ እንዲሆን እንዲሁም ከከንፈርና ከድድ አቀማመጥ ጋር የተጣጣመ ውብ ፈገግታ እንዲኖራቸው የሚደረግ የውበት ሕክምና ነው።
የሕክምናው ስያሜም በሆሊውድ ፊልሞች ላይ የሚታዩ ተዋንያን ካላቸው ማራኪ የጥርስ አቀማመጥና ፈገግታ ጋር ተያይዞ የመጣ እንደሆነ ዶክተሯ አውስተዋል።

ይህ ሕክምና በተለይ በተለያዩ ምክንያቶች ማለትም በውኃ፣ በመድኃኒት ወይም በኢንፌክሽን ሳቢያ የጥርስ ቀለማቸው ለተቀየረና ጥርሳቸውን ነጭ ለማድረግ ለሚፈልጉ ግለሰቦች በእጅጉ ይመከራል።
በተጨማሪም ከሥራቸው ባህሪ አንጻር ከሰዎች ጋር የቅርብ ግንኙነት ላላቸው እንደ ታዋቂ ሰዎችና የፊልም ባለሙያዎች፣ እንዲሁም በአጠቃላይ በራስ የመተማመን ስሜታቸውን ከፍ ማድረግ ለሚሹ ሰዎች ሁሉ ተመራጭ መሆኑን ዶክተር ሳውዳ ገልጸዋል።
ወደ ሆሊውድ ስማይል ሕክምና ከመገባቱ በፊት የጥርስ ጤንነት አስቀድሞ መረጋገጥ እንዳለበት ያሳሰቡት ዶክተሯ፤ ይህም ኢንፌክሽን አለመኖሩን ማረጋገጥን፣ የተበሳ ወይም የተሰበረ ጥርስ ካለ አስቀድሞ ማከምን እንደሚጨምር ገልጸዋል።
ሕክምናው በኤክስሬይ እንዲሁም በ3D ስካን ካሜራዎች የታካሚውን የጥርስ አወቃቀር አይቶ ተገቢውን ዲዛይን በማድረግ የሚከናወን መሆኑንም አስረድተዋል። ይሁን እንጂ ሕክምናው የራሱ የሆኑ ተጓዳኝ ጉዳቶች ሊኖሩት እንደሚችሉ ዶክተር ሳውዳ ጠቁመዋል።

ለምሳሌ ሕክምናው በሚሰራበት ወቅት የተወሰነ የጥርስ ክፍል ስለሚፋቅ፤ ቀዝቃዛ ወይም ትኩስ ነገር ሲወሰድ የጥርስ ስሜት መለወጥ (Sensitivity) ሊኖር እንደሚችልና አልፎ አልፎም የድድ መቆጣት ሊከሰት እንደሚችል ገልጸዋል።
በአመጋገብ ረገድም እንደ ቆሎ እና አጥንት ያሉ በጣም ጠንካራ የሆኑ ምግቦችን መመገብ ሰው ሰራሽ ጥርሱ ላይ የመሰበር አደጋ ሊያመጣ ስለሚችል ከፍተኛ ጥንቃቄ እንደሚያስፈልገው አሳስበዋል።
ሕክምናው ዘላቂ ባለመሆኑም እንደ አጠቃቀሙ ሁኔታ ከ10 እስከ 15 ዓመታት ባለው ጊዜ ውስጥ ሙሉ በሙሉ መቀየር ሊያስፈልገው እንደሚችል ጠቅሰዋል።
ዶክተር ሳውዳ በማጠቃለያቸውም፣ ተፈጥሯዊ ጥርስን ተንክብክቦ መያዝ ቀዳሚ ምርጫ ቢሆንም፤ በተለያዩ ምክንያቶች በራስ የመተማመን ስሜታቸው ለቀነሰና ማራኪ ፈገግታ ለሚሹ ሰዎች ይህ ሕክምና ውጤታማ አማራጭ መሆኑን አስታውቀዋል።
በበረከት ጌታቸው