AMN – መጋቢት 23/2018 ዓ.ም
የወደፊቷ ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን የቻለችና በቴክኖሎጂ የበለጸገች እንድትሆን መሰረቱ ዛሬ በፈጠራ ሰሪዎቻችን እጅ እየተጣለ ነው።
ከኤ ኤም ኤን ጋር ቆይታ ያደረገው በለሚ ኩራ ማኑፋክቸሪንግ ኮሌጅ ለስምንት አመታት የሚጠጋ የስራ ልምድ ያለው አሰልጣኝ ጌትነት ጋሎ፣ የከተማ ግብርናን ወደ ላቀ ምዕራፍ የሚያሸጋግር የመኖ መቆራረጫ ማሽን ለአገልግሎት አብቅቷል።
ይህ ማሽን ተራ የብረት ስብስብ አይደለም፤ ይልቁንም የከተማ ግብርናን ተግዳሮቶች በብልሃት የሚፈታ የቴክኖሎጂ ውጤት እንጂ፡፡
ማሽኑ የእንስሳት መኖን በቀላሉ በመቆራረጥ ለምገባ አመቺ ከማድረግ ባለፈ የዛፍ ቅርንጫፎችን በቀላሉ በመቆራረጥ ጥራት ያለው ኮምፖስት ለማዘጋጀትም እንደሚያገለግል አሰልጣኝ ጌትነት ተናግሯል፡፡
አሰልጣኝ ጌትነት የሰራው ማሽን ከውጭ ለማስገባት እስከ 218 ሺ ብር እንደሚጨርስ ገልፆ፣ በሀገር ውስጥ ጥሬ እቃና እውቀት የተሰራው ማሽን ግን በ165 ሺ ብር ጠቅላላ ዋጋ እንደተጠናቀቀ እና ለገበያ እንደቀረበ ተናግሯል፡፡
ሀገራችን በራሷ ምርት ራሷን መቻል ስላለባት ልምምድ እያደረግን ነው የሚለው አሰልጣኝ ጌትነት፣ ይህ ጅማሮ ለነገዋ ኢትዮጵያ ተስፋ ሰጪ እንደሆነም አመላክቷል፡፡
ማሽኑ በአሁኑ ወቅት በለሚ ኩራ ማኑፋክቸሪንር ስር ላሉ በከብት እርባታ ላይ ለተሰማሩ ኢንተርፕራይዞች አገልግሎት እየሰጠ ሲሆን፣ ወደፊትም በየቤቱ ለሚደረግ የከተማ ግብርና ትልቅ ተስፋ እንደሚሆን አሰልጣኝ ጌትነት ገልጿል፡፡
በአስማረ መኮንን