AMN-ሚያዝ 15/2018 ዓ.ም
ከሀገራዊ ለውጡ በፊት አዲስ አበባ በመኪና ጭስና በንግድ ግርግር ብቻ ትታወቅ ነበር፤ዛሬ የከተማዋ ገጽታ ብቻ ሳይሆን የሀገሪቱ የልብ ትርታም ተቀይሯል።
በታላቁ ቤተ መንግሥት አቅራቢያ የሚገኘውና የቀለበት ቅርፅ ያለው የሳይንስ ሙዚየም ሲታይ፣ ኢትዮጵያ ከታሪካዊ የጥበብ ማማነቷ ባሻገር የነገውን ዓለም ለመምራት መነሳቷን ያበስራል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ “ዲጂታል ኢትዮጵያ 2025” የተሰኘው ታላቅ ራዕይ የሀገሪቱን የልማት አቅጣጫ ወደ አዲስ ምዕራፍ አሸጋግሮታል።
ሳይንስና ቴክኖሎጂ ከመንግሥት አምስቱ የብልጽግና ምሰሶዎች አንዱ ተደርጎ የተወሰደ ሲሆን፣ይህ ጉዞ ከምድር አቧራ ተነስቶ እስከ ጠፈር ምህዋር የተዘረጋም ነው።
ኢትዮጵያ ከዓመታት በፊት የኤ.አይ ኢንስቲትዩትን ስታቋቁም በአፍሪካ ተቋሙን በገለልተኛነት የመሰረተች ብቸኛ ሀገር ሰትሆን አሁን ግን ይህ ራዕይ ወደ ላቀ ደረጃም ተሸጋግሯል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቅርቡ እንዳበሰሩት ኢትዮጵያ በዓለማችን ሁለተኛ የሆነውን የኤ.አይ ዩኒቨርስቲ በመገንባት ላይ ትገኛለች።

በወራት ውስጥ ስራ የሚጀምረው ይህ ተቋም በአፍሪካ ፈር ቀዳጅ ከመሆኑም ባለፈ፣የኤ.አይ ቴክኖሎጂ ራሱ የዩኒቨርሲቲው የቦርድ አባል ሆኖ እንዲያገለግል መታቀዱ ሀገሪቱ ለዘመኑ ሳይንስ የሰጠችውን ልዩ ትኩረት ያሳያል።
የሳይንስ ሙዚየሙ የዚህ ሽግግር ቁሳዊ ምስክር ሲሆን፣ለሀገሪቱ ወጣቶች “የማይቻል ነገር የለም” የሚል ተስፋ የሚዘራ የሀሳብ ፋብሪካም ሆኗል።
መንግሥት ለፈጠራ ስራዎች ካለው ቁርጠኝነት የተነሳም፣ ስታርታፖችን ለመደገፍ ልዩ ሕንፃ በማስገንባት ወጣት የቴክኖሎጂ ፈጣሪዎችን እያበረታታ ይገኛል።
በዚህም ብቻ ያላበቃው የቴክኖሎጂ ጉዞ ኢትዮጵያ አይኖቿን ወደ ሰማይም እንድትመለከት ያስቻለ ሲሆን፣ ኢትዮጵያ የራሷን ሳተላይቶች ወደ ጠፈር እንድታመጥቅ በማድረግ ረገድ ትልቅ እምርታ ታይቷል።

በጠቅላይ ሚኒስትሩ አነሳሽነት የተመሰረተው የስፔስ ሳይንስ ኢንስቲትዩት፣ ET-RSS1 እና ET-SMART-RSS የተሰኙ ሳተላይቶችን ወደ ጠፈር ማምጠቅ ተችሏል።
ይህ ስኬት በምድር ላይም በሚሊዮን የሚቆጠሩ ወጣቶችን በዲጂታል ክህሎት ከማብቃት ጋር ተጋምዷል።
የ”5 ሚሊዮን ኮደሮች” ፕሮጀክት ኢትዮጵያን በአፍሪካ የቴክኖሎጂ ተሰጥኦ ለማድረግ የታለመ ግዙፍ ስትራቴጂ ነው።
ከዚህም ባለፈ የቴሌኮም ዘርፉ ለውጭ ኢንቨስተሮች ክፍት መሆኑና የ5G አገልግሎት መጀመር የኢንተርኔት ተደራሽነትን በከፍተኛ ደረጃ አሳድጓል።
እንደ ቴሌብር ያሉ ውጤቶች ደግሞ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዜጎችን ወደ ዘመናዊው የፋይናንስ ስርዓት አስገብተዋል።
ዛሬ ላይ የጠቅላይ ሚኒስትሩ እሳቤ ኢትዮጵያን ከአፍሪካ ቀዳሚ የዲጂታል ተዋናይ ለማድረግ የጀመረችውን ጉዞ አፋጥኖታል።

ከምናባዊ እሳቤ የተነሳው ራእይ ከሳይንስ ሙዚየም እስከ ስፔስ ሳይንስ፣ ከስታርታፕ ድጋፍ እስከ ዓለማችን ሁለተኛው የኤ.አይ ዩኒቨርሲቲ ድረስ ኢትዮጵያ በቴክኖሎጂ የታገዘ ብልጽግናን ለማምጣት ዘመኑን ዋጅታለች።
በሚካኤል ህሩይ