ትዕግስት አሰፋ እና ታምራት ቶላ በለንደን ማራቶን ይጠበቃሉ

You are currently viewing ትዕግስት አሰፋ እና ታምራት ቶላ በለንደን ማራቶን ይጠበቃሉ

AMN -ሚያዝያ 16/2018 ዓ.ም

በወርልድ አትሌቲክስ የፕላቲንየም ደረጃ የተሰጠው የለንደን ማራቶን የፊታችን እሁድ ለ46ኛ ጊዜ ይከናወናል፡፡

ዓለማቀፋዊነቱ እየሰፋ በመጣው በዚህ ውድድር ላይ በርከት ያሉ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ተሳታፊ እንደሚሆኑ የውድድሩ አዘጋጆች ይፋ አድርገዋል፡፡

በሴቶች የባለፈው ዓመት አሸናፊዋ ትዕግስት አሰፋ ዘንድሮም የበላይነቱን ትወስዳለች የሚል ቅድመ ግምት ተሰጥቷታል፡፡

አትሌቷ በ45ኛው የለንደን ማራቶን ያስመዘገበችው 2:15:50 ሰዓት ታሪክ የሰራችበት ነበር፡፡

ያለምንም ወንድ አሯሯጭ በሴቶች ብቻ በተደረገው በዚህ ውድድር የተመዘገበው ሰዓት የዓለም ክብረወሰን ተብሎ ተመዝግቦላታል፡፡

የኦሊምፒክ እና የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና የብር ሜዳልያ ባለቤቷ ትዕግስት አሰፋ የግል ምርጥ ሰዓቷ በ2023 የበርሊን ማራቶን ላይ ያስመዘገበችው 2:11:53 ነው፡፡ ’’ባለፈው ዓመት ክብረወሰን በማሻሻል ያስመዘገብኩት ውጤት በአትሌቲክስ ሕይወቴ ከምኮራባቸው ውጤቶች አንዱ ነው ፤ ዘንድሮም ይህን መድገም እፈልጋለሁ’’ በማለት ከሩጫው በፊት በነበራት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ተናግራለች፡፡

ከትግስት አሰፋ ውጪ ደጊቱ አዝመራው እና ባለምላይ ሹመት ጥሩ ተፎካካሪ ይሆናሉ ተብሎ የሚጠበቁ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ናቸው፡፡ ኬንያውያኑ ጆይስሊን ጄፕጎስኪ እና ሄለን ኦብሪ የትግስት አሰፋ ተፎካካሪዎች እንደሚሆኑ የወርልድ አትሌቲክስ ዘገባ ግምቱን አስቀምጧል፡፡

በወንዶች የኦሊምፒክ እና የዓለም አትሌቲክስ የወርቅ ሜዳልያ ባለቤቱ ታምራት ቶላ ተጠባቂ ሆኗል፡፡ አትሌቱ በለንደን ማራቶን ሲሳተፍ የእሁዱ ለአምስተኛ ጊዜው ይሆናል፡፡ ታምራት ቶላ በተያዘው ዓመት ባደረገው የዶሃ ማራቶን 2:05:40 በሆነ ሰዓት መሸነፉ ይታወሳል፡፡

ዮሚፍ ቀጀልቻ ሌላኛው ተጠባቂ ኢትዮጵያዊ አትሌት ነው፡፡ ሙሉ ለሙሉ በሚያስብል ሁኔታ ወደ ጎዳና ሩጫ ፊቱን ያዞረው ዮሚፍ ሙሉ ማራቶን ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ ይወዳደራል፡፡ በማራቶን የምንጊዜም ዘጠነኛ ፈጣን ሰዓት ባለቤቱ ደሬሳ ገለታም ይጠበቃል፡፡

የ2025ቱ የለንደን ማራቶን አሸናፊው ኬንያዊው ሰባስቲያን ሳዌ እንዲሁም ዩጋንዳዊው ጃኮብ ኪፕሊሞ የኢትዮጵያውያን አትሌቶች ዋነኛ ተፎካካሪዎች ናቸው፡፡

በሸዋንግዛው ግርማ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review