AMN – ሚያዝያ 17/2018 ዓ.ም
የኢትዮጵያ እና የደቡብ ሱዳን ግንኙነት ከጎረቤትነት ባለፈ በአፍሪካ ቀንድ አስተማማኝ ሰላም እና የኢኮኖሚ ውህደትን ለማምጣት ወሳኝ መሆኑ ይነገራል።
ባለፉት ጥቂት አመታት በሁለቱ ሀገራት መሪዎች መካከል የታየው ቁርጠኝነት ግንኙነቱን ከዲፕሎማሲያዊ ንግግሮች ባለፈ ወደ ተጨባጭ የመሰረተ ልማት እና ሌሎች ዘርፈ ብዙ ትብብር አሸጋግሮታል።
ሁለቱ ሀገራት የጋራ ድንበራቸውን ከስጋት ነጻ ለማድረግ በወሰዱት እርምጃ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ እና የደቡብ ሱዳን ብሔራዊ ፖሊስ የመግባቢያ ስምምነት መፈራረማቸው ይታወሳል።
ይህም ህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርን እና የጦር መሳሪያ ኮንትሮባንድን ለመቆጣጠር የሚደረገው የጋራ ኦፕሬሽን ለቀጣናው ደኅንነት ቁልፍ ሚና አለው።
በደቡብ ሱዳን የሚገኘው የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪ ኃይል ለህዝቦች ደኅንነት እየከፈለ ያለው መስዋዕትነት እና ያሳየው ውጤታማነትም ዓለም አቀፍ ሜዳሊያ ያስገኘ ሲሆን ይህም ኢትዮጵያ ለደቡብ ሱዳን ሰላም ያላትን ጽኑ አቋም ያሳያል።
ሌላው በ2015 ዓ.ም ኢትዮጵያ እና ደቡብ ሱዳን የድንበር ተሻጋሪ የፓሎች-ማቲያንግ-ማይውት-ፓጋክ የመንገድ ግንባታ ስምምነት ተፈራርመዋል።
የመንገድ ግንባታው የሁለቱን ሀገራት ዋና ከተሞች የሚያገናኝ የ220 ኪሎ ሜትር የፍጥነት መንገድ ሲሆን ሀገራቱን በመሰረተ ልማት የሚስተሳስር፣ ለንግድ እና ኢንቨስትመንት መደላድል የሚፈጥር ነው ፡፡

በሌላ በኩል ደቡብ ሱዳን ለኢትዮጵያ የልማት ፕሮጀክቶች ያላት ግልጽ አቋም በተለይም በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ አሳይታለች፡፡
የዓባይ ተፋሰስ የትብብር ማዕቀፍ ስምምነትን (CFA) በማጽደቅ የዓባይ ውሃን በፍትሐዊነት እና በምክንያታዊነት ለመጠቀም ያላቸውን ጽኑ አቋም ካሳዩ አገራት አንዷ ደቡብ ሱዳን ናት፡፡
እ.አ.አ በነሐሴ 2022 የደቡብ ሱዳን ከፍተኛ ልዑካን ቡድን ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን በአካል ተገኝቶ መጎብኘቱ፣ ፕሮጀክቱ ከመደገፍ ባለፈ ግድቡ ለቀጣናው ያለውን ጠቀሜታ መረዳት እና የቀጣናዊ ትስስርን አስፈላጊነትን ያረጋገጠ ሆኗል።
እንዲሁም በኤሌክትሪክ ኃይል እና በነዳጅ አቅርቦት ዙሪያ በጋራ መስራታቸው ግንኙነታቸው የጋራ ተጠቃሚነት ላይ መሰረት ያደረገ መሆኑን ሌላኛው ማሳያ ነው።
የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት በመንግስታት ደረጃ ብቻ ሳይሆን በህዝብ ለህዝን ግንኙነት የተጠናከ ነው።

ኢትዮጵያ ለደቡብ ሱዳናውያን ወጣቶች በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ የምትሰጠው ነፃ ትምህርት ዕድል የወደፊቷን የአፍሪካ መሪዎች በአንድነት የማነጽ አንዱ አካል ነው።
እንዲሁም ለደቡብ ሱዳን ስደተኞች የምታደርገው ሰብዓዊ አቀባበል እና ከድንበር አካባቢ ህዝቦች ጋር ያለው የንግድ እና የባህል ትስስር ለቀጣናው ሰላም ትልቅ ዋጋ አለው።
የደቡብ ሱዳን ፕሬዝደንት ሳልቫኬር ማያርዲትን በርካታ መሪዎች እያቀኑባት ወዳለችው የዲምሎማሲ ማዕከሏ አዲስ አበባ ይፋዊ የስራ ጉብኝት አድርገዋል።
ጉብኝቱን ተከትሎ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) እና ፕሬዝደንት ሳልቫኬር ያደረጉት የሁለትዮሽ ውይይትም የሁለቱን ሀገራት የኢኮኖሚ ትስስር በኢንቨስትመንት ለመደገፍ ትልቅ አቅጣጫ ያስቀመጠ ነው፡፡
በትዝታ መንግስቱ