AMN – ሚያዝያ 29/2018 ዓ.ም
የኩላሊት መድከም በዓለም አቀፍ ደረጃ የብዙዎችን ሕይወት የሚቀጥፍ ስጋት እየሆነ በመምጣቱ፣ ኅብረተሰቡ አስቀድሞ ተገቢውን ጥንቃቄ ሊያደርግ እንደሚገባ የጤና ባለሙያዎች መክረዋል።
የኩላሊት ሕክምና ስፔሻሊስት የሆኑት ዶ/ር ተስፋዬ ይልማ እንደሚገልፁት፤ ኩላሊት በሰውነታችን ውስጥ መርዛማ ዝቃጮችን የማስወገድና የማዕድናትን መጠን የማመጣጠን ከፍተኛ ኃላፊነት ያለበት ውስብስብ አካል ነው።
ለበሽታው መባባስ ዋነኛውን ድርሻ የሚይዙት ከቁጥጥር ውጭ የሆነ የስኳር በሽታ እና ከፍተኛ የደም ግፊት ቢሆኑም፣ ሌሎች ተጓዳኝ ምክንያቶችም ለኩላሊት ሥራ ማቆም ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረክታሉ።

ከእነዚህም መካከል ያለ ሐኪም ትዕዛዝ የሚወሰዱ እንደ “አይቡፕሮፌንና ዲክሎፌናክ”ያሉ የሕመም ማስታገሻዎች፣ ተደጋጋሚ የሽንት ቧንቧ ኢንፌክሽን፣ ከልክ ያለፈ ውፍረትና ሲጋራ ማጨስ በዋነኝነት ይጠቀሳሉ።
አደገኛ የሆነውን የጤና ቀውስ ለመከላከል ግለሰቦች በቂ ውኃ የመጠጣት ልምድን ሊያዳብሩና በምግብ ውስጥ የጨው አጠቃቀምን በመቀነስ የደም ግፊታቸውን ሊያረጋጉ ይገባል።
ከዚህም በተጨማሪ አትክልትና ፍራፍሬን ማዘውተር፣ የተቀነባበሩ ምግቦችን ማስወገድና በቀን ቢያንስ ለሠላሳ ደቂቃ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ ለኩላሊት ጤንነት ዋስትና እንደሚሰጡ ባለሙያው አስገንዝበዋል።
የኩላሊት ሥራ በከፍተኛ ሁኔታ ተዳክሞ ከ15 በመቶ በታች በሚደርስበት ወቅት፣ ሕመሙ “የመጨረሻ ደረጃ የኩላሊት ድካም” ወደሚባለው አደገኛ ምዕራፍ ይሸጋገራል።

በዚህ ወቅት ኩላሊት በራሱ አቅም ደምን ማጣራትና ትርፍ ፈሳሽን ማስወገድ ስለማይችል፣ የኩላሊት እጥበት ወይም የንቅለ ተከላ ሕክምና የግድ ይላል።
የኩላሊት እጥበት የታካሚውን ዕድሜ ለማራዘም የሚረዳ የቆይታ ሕክምና እንጂ የታመመውን ኩላሊት ሙሉ በሙሉ የሚፈውስ ባለመሆኑ፣ ለችግሩ ዘላቂ መፍትሔ የሚሆነው የኩላሊት ንቅለ ተከላ ማድረግ መሆኑን ዶ/ር ተስፋዬ አስገንዝበዋል።
በመሆኑም እንደ እግር እብጠት፣ የሽንት መልክ መቀየር፣ ከፍተኛ ድካም ወይም የማቅለሽለሽ ስሜት ያሉ ምልክቶች ሲታዩ በአፋጣኝ ወደ ሕክምና ተቋም ማምራት ያስፈልጋል።
በተለይም የስኳርና የደም ግፊት ታካሚዎች በሽታው ሳይባባስ አስቀድሞ ለመከላከል በየዓመቱ የኩላሊት ተግባር ምርመራ ሊያደርጉ እንደሚገባ ተመክሯል።
በበረከት ጌታቸው