AMN ሚያዝያ 28/2018 ዓ.ም
በመጀመሪያው የአፍሪካ ማህበራዊ ሚዲያ ተጽዕኖ ፈጣሪዎች ጉባኤ (ASMIS 2026) ላይ ለመሳተፍ፣ ከ30 የአፍሪካ ሀገራት የተወጣጡና በአጠቃላይ 321 ሚሊዮን ተከታዮች ያሏቸው 61 ታዋቂ ተጽዕኖ ፈጣሪዎች ወደ አዲስ አበባ መግባት ጀምረዋል።
እነዚህንም 150 ሚሊዮን ተከታዮች ያሏቸው 120 ታዋቂ ኢትዮጵያውያን የማህበራዊ ሚዲያ የይዘት ፈጣሪዎች ይቀላቀሏቸዋል።
ታሪካዊው ጉባኤ ነገ እና ከነገ በስቲያ በአድዋ ድል መታሰቢያ ይካሄዳል።
ጉባኤው በፐልስ ኦፍ አፍሪካ ሚዲያ እና በኤጂኤ ቴክ ኢንተርፕራይዝ የጋራ ትብብር የተዘጋጀም ነው።
በአፍሪካ የዲፕሎማሲ ማዕከል አዲስ አበባ የሚካሄደው ይህ ጉባኤ የአፍሪካን ዲጂታል የወደፊት ዕጣ ፈንታ እንደገና ለመቅረጽ ያለመ ነው።
ጋናዊው ታዋቂ ዩቲዩበር እና የዲጂታል ሚዲያ ተጽእኖ ፈጣሪ በርትሆልድ ኮቢ ዊንክለር አክኮን (ዎዴ ማያ በብዙዎች ዘንድ የሚታወቅበት ስም ነው) ዛሬ ማለዳ አዲስ አበባ ገብቷል።

ሴራሊዮናዊው ቦይዜ ክሪሽ፣ ቤኒናዊው ሬጌ ቦይዘር፣ ሴኔጋላዊው ጃው ኬቹፕ እና ስዊዛላንዳዊው ጎጎ እስዋቲኒ ኤምኤም ሌሎች ለጉባኤው የገቡ የዲጂታል ሚዲያ ተጽእኖፐ ፈጣሪዎች ናቸው።
የማህበራዊ ሚዲያ ተፅእኖ ፈጣሪዎቹ በቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ አቀባበል እየተደረገላቸው ይገኛል።
ጉባኤው በአፍሪካ ያሉ ተጽዕኖ ፈጣሪዎች የሚሰባሰቡበት፣ ስለራሳቸውና ስለ አፍሪካ የሚናገሩበት፣ እንዲሁም ስለ ይዘት ፈጠራና ስለሚገጥሟቸው ተግዳሮቶች የሚወያዩበት መድረክ ነው።
ይህም ተጽእኖ ፈጣሪዎቹን በአንድ መድረክ የማገናኘት ትልቅ አጋጣሚን ፈጥሯል።
ሰው ሰራሽ አስተውሎት (AI) በመጠቀም የይዘት ፈጣሪነት የወደፊት ሁኔታ፣ የአፍሪካ አዎንታዊ ገጽታን መገንባት እና የዲጂታል ተጽዕኖን ከአፍሪካ ህብረት የ2063 አጀንዳ ጋር ማጣጣም በሚሉ ጉዳዮች ላይ ሶስት የከፍተኛ ደረጃ የፓናል ውይይቶች ይካሄዳሉ።
ጉባኤው “በችግር ላይ የተመሰረተ” ዘገባን በእውነተኛ የአፍሪካ የዕድገት ታሪኮች ለመተካት የታለመ ስትራቴጂካዊ እርምጃ መሆኑም ተመልክቷል።

የአፍሪካ ማህበራዊ ሚዲያ ተጽእኖ ፈጣሪዎች ጉባኤ የኢትዮጵያን ቱሪዝም በከፍተኛ ሁኔታ የማስተዋወቅ እድሉ ሰፊ ነው።
እነዚህ የይዘት ውጤቶች የአፍሪካን መልካም ገጽታ ለዓለም፣ የኢትዮጵያንም መልካም ገጽታ ለአፍሪካውያን ማሳየት የሚችሉ መሆናቸዉን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
ጉባኤው ሐሙስ ዕለት በዓድዋ ድል መታሰቢያ ሙዚየም የሚጀመር ሲሆን፣ ከ470 ሚሊዮን በላይ የዲጂታል ተከታዮች አይኖች በአሁኑ ወቅት በአዲስ አበባ ላይ አርፈዋል።
ይህም አፍሪካ የራሷን ታሪክ ራሷ መተረክ የጀመረችበት አዲስ ዘመን ማሳያ ሆኗል።