AMN ሚያዝያ 29/2018 ዓ.ም
የኢትዮጵያ የሙዚቃ ንጉስ ተብለው የሚጠሩ፣ ስማቸው በትዝታ ሙዚቃዎች የሚታወቀው እና፣ በሀገሪቱ የሙዚቃ ታሪክ ውስጥ አሻራቸውን መጣል ከቻሉ ዝነኛ ድምፃዊያን መካከል አንዱ መሃሙድ አህመድ ነው።
ስመ ጥሩ ድምፃዊ መሃሙድ አህመድ በ1933 ዓ/ም በአዲስ አበባ ከተማ አሜሪካን ግቢ አካባቢ ተወለደ፡፡
ሥራንም ሆነ ሕይወትን በራሱ መጋፈጥ የጀመረው ገና በሕፃንነቱ ነው፡፡ አባቱ በሚሠራበት ግሪክ ክለብ አብሮ በመሔድ ቅርጫት ኳስና የቴኒስ ሜዳዎቹ ላይ ይሠራም ነበር፡፡
በስድስት ዓመቱም ሊስትሮ ሆኖ መሥራት ጀመረ፡፡ የሙዚቃ ሕይወቱ ሀ ብሎ የተጀመረው አንድ ክለብ ውስጥ ሳንድዊች እንዲያቀርብ በተቀጠረበት ጊዜ ነዉ፡፡ እንደ አጋጣሚም ሆኖ በዚያው ክለብ ውስጥ ጥላሁን ገሠሠ ይዘፍንበት የነበረ ቦታ ነበር፡፡
የኢትዮጵያ የስነ ጥበባትና የመገናኛ ብዙሃን ታህሳስ 24 ቀን 1991 ዓ/ም ድምጻዊዉን ”የረጅም ጊዜ ተሸላሚ” በሚል ዘርፍ ሸልሞታል፡፡
ከ80 በላይ በጉራጊኛና በአማርኛ የዘፈነው መሃሙድ አህመድ ተደናቂነትን ካተረፈባቸው ሥራዎቹ መካከል የሺ ሀረጊቱ፣ መቼ ነው ሀገሬን የማየው፣ አሽቃሩ፣ ኢትዮጵያና የሠላሌዋ በዋናነት ይጠቀሳሉ፡፡

ድምፃዊው በሱ ዘመን ካሉት ድምፃዊያን በተሻለ መልኩ በውጭ ሀገራት በተለያዪ መድረክ ስራዎቹን በማቅረቡ ቢቢሲ በ1999 ዓ/ም “ከአፍሪካ የአለም አቀፍ የሙዚቃ ተሸለሚ” በሚል የሚታወቀውን የሽልማት ዘርፍ አበርክቶለታል፡፡
በ1963 ከአይቤክስ ባንድ ጋር ራስ ሆቴል በሚሠራበት ወቅት ‹‹ኩሉን ማን ኳለሽ››፣ ‹‹አምባሰል››፣ ‹‹ችቦ አይሞላም ወገቧ›› እና ‹‹አልማዝ ምን ዕዳ ነው›› የመሳሰሉ ዘፈኖችን ይዘፍን ነበር፡፡
እነዚህ ዘፈኖች ከአንዳንድ ወገኖች ከፍተኛ ትችትም አጋጠመው፡፡

የዱሮ ዘፈኖችን በአዲስ መልክ ትጫወታለህ በማለት አንድ ጋዜጠኛ ‹‹ፍራሽ አዳሽ›› ብሎ የጠራውን አጋጣሚም አሁንም አይረሳውም፡፡ እሱም አለማዘኑን ገልፆ መልሶም የዱሮ ዘፈኖችን አዲስ ሕይወት በመስጠት ዘፍኛለሁ፡፡ ፍራሽም እንደ አዲስ ሲታደስ ይተኛበታል›› ይላል፡፡
በኢትዮጵያውያን ዘንድ ተወዳጅነትን፣ ተደናቂነትን፣ ተፈቃሪነትን ማትረፍ የቻለ ፈርጥ እንደሆነ ብዙዎች ያምናሉ፡፡ ሙሉ ሕይወቱን በሙዚቃ ያሳለፈው መሃሙድ በሙዚቃው ይተነፍሳል፣ ይናገራል፣ ሰውን ያዝናናል፡፡ ከአርባ ዓመታት በላይ በቆየውም የሙዚቃ ሕይወቱ ትውልዱን በሙዚቃው ማስተሳሰር የቻለ ታላቅ አርቲስት ነው፡፡
በተለያዩ ኮንሠርቶች በሚዘፍንበትም ወቅት በተለያዩ ዕድሜ ክልል የሚገኙ ሰዎች ብሔራዊ መዝሙር በሚመስል መልኩ አብረውት በመዝፈንም በዘፈኑ አንድነትን ያሳያሉ፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርም ድምጻዊዉ ላበረከተዉ የላቀ አስተዋጽኦ ለትዉልዱ መማሪያ ይሆን ዘንድ የክብር ሃዉልት አቆሞለታል።
በምህረት ይልማ