AMN – ሚያዝያ 29/2018 ዓ.ም
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሕፃናት ከፅንሰት ጀምሮ እስከ ስድስት ዓመት ባለው የዕድሜ ክልል ውስጥ ተገቢውን እንክብካቤ እንዲያገኙ ለማስቻል የቀረጸው “የቀዳማይ ልጅነት ልማት ፕሮግራም” ለውጥ እያስመዘገበ ይገኛል።
መርሐ-ግብሩ በተለይ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን የኅብረተሰብ ክፍሎች ተጠቃሚ ከማድረጉም ባለፈ፣ መዲናዋን ለሕፃናት ሁለንተናዊ ዕድገት ምቹ የማድረግ ግብን አንግቦ እየተተገበረ ነው።
አስተዳደሩ በከተማዋ 11ዱም ክፍለ ከተሞች ሕፃናት ቦርቀው የሚጫወቱባቸውና ማህበራዊ ትስስርን የሚለማመዱባቸው ከ5 ሺህ በላይ የልጆች መጫወቻ ስፍራዎችን ገንብቶ ለአገልግሎት አብቅቷል።

በተጨማሪ ወላጆች ልጆቻቸውን የሚያውሉበት ቦታ እንዳይቸገሩ ለማድረግ ከ1ሺህ በላይ የሕፃናት ማቆያዎች (ዴይ ኬር) ተገንብተው በርካታ ወላጆችንና ሕፃናትን ተጠቃሚ ማድረግ ችለዋል።
እናቶች በሥራ ገበታቸው ላይ ሆነው ልጆቻቸውን በቅርበት እንዲንከባከቡና በሥራቸው ላይ ሙሉ ትኩረት እንዲያደርጉ የሚያስችሉ 713 የሕፃናት ማቆያዎች የፊዴራል ተቋማትን ጨምሮ የተደራጁ ሲሆን፣ በአጠቃላይ በከተማዋ ከ11 ሺ በላይ ሕፃናት በማቆያዎቹ ውስጥ አገልግሎት በማግኘት ላይ እንደሚገኙ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሴቶችና ሕፃናት ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ቆንጅት ደበላ ለኤ ኤም ኤን ገልፀዋል።

ይህ የትውልድ ቀረፃ ስራ ሕፃናት ወደ መደበኛ ትምህርት ከመግባታቸው በፊት ተገቢውን የህይወት ጅማሬ እንዲኖራቸውና ሀገራቸውን መጥቀም በሚችሉበት ሁኔታ እንዲያድጉ ምቹ ሁኔታዎችን እየፈጠረ ይገኛል።
የሕፃናቱን የምግብ ድጋፍ ማጠናከር እና ደህንነቱ የተጠበቀ የመጫወቻና የመዝናኛ ስፍራዎችን በየሰፈሩ ማስፋፋት፣ የዛሬ ሕፃናት በጤናማ ሁኔታ አድገው የነገዋን ከተማ እንዲረከቡ የታሰበ የአዲስ አበባ አስተዳደር ትጋት ማሳያ ተደርጎ ይወሰዳል።
ለፕሮግራሙ ስኬታማነት ሲባል ሳይወሰን፣ አገልግሎቱን እስከ ግለሰብ ቤት ድረስ ለማድረስ 5 ሺህ ባለሙያዎች አስፈላጊው ስልጠና ተሰጥቷቸው በሁሉም የከተማዋ ክፍሎች ተሰማርተዋል።

እነዚህ ባለሙያዎች ቤት ለቤት በመሄድ ለሕፃናትና ለወላጆች የቅርብ ምክርና ድጋፍ በመስጠት ላይ ይገኛሉ። በተጨማሪም በማቆያዎቹ ውስጥ ሕፃናቱን የሚንከባከቡ ባለሙያዎች በሥነ-ልቦና እና በሕፃናት አያያዝ የሰለጠኑ በመሆናቸው፣ ሕፃናቱ ጨዋታን መሠረት ያደረገ ትምህርት እንዲያገኙ አስችሏቸዋል።
ይህ የተቀናጀ ተግባር የሴቶችን የሥራ ተሳትፎና ምርታማነት ከማሳደጉም በላይ፣ ሕፃናቱ ወደ መደበኛ ትምህርት ከመሸጋገራቸው በፊት አስፈላጊውን አካላዊና ሥነ-ልቦናዊ ዝግጅት እንዲያደርጉ አስችሏል።
በበረከት ጌታቸው