የምርጫ ቁሳቁሶች ወደ ምርጫ ጣቢያዎች እየተሰራጩ ነው

AMN ግንቦት 21/2018

በሐረሪ ክልል የምርጫ ቁሳቁስ ወደ ምርጫ ጣቢያዎች እየተሰራጨ መሆኑን በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የክልሉ ምርጫ ጽህፈት ቤት አስታወቀ።

በኢትዮጵያ የምርጫ ታሪክ በርካታ መራጮች የምርጫ ካርድ የወሰዱበት 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የፊታችን ሰኞ ይካሄዳል።

ለምርጫው በሁሉም ረገድ የተሟላ ዝግጅት የተደረገ ሲሆን በየምርጫ ጣቢያዎችም የምርጫ ቁሳቁሶች ተጓጉዘው ተደራሽ እየተደረጉ ነው።

በዚሁ መሰረትም በሐረሪ ክልል የምርጫ ቁሳቁስ ወደ ምርጫ ጣቢያዎች እየተሰራጨ መሆኑን በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የክልሉ ምርጫ ጽህፈት ቤት አስተባባሪ አቶ ጌታቸው ቦጋለ ገልጸዋል።

በሁሉም የምርጫ ጣቢያዎች ለድምፅ አሰጣጡ ሂደት መሳካት የተሟላ ዝግጅት መደረጉን የተናገሩት አስተባባሪው፥ የምርጫ ቁሳቁሶች በመሰራጨት ላይ መሆኑን ተናግረዋል።

የድምጽ መስጫ ወረቀትን ጨምሮ ሌሎችም አስፈላጊ የምርጫ ቁሶች ወደ ምርጫ ጣቢያዎች በመሰራጨት ላይ መሆናቸውን አንስተው፥ ቦርዱ በተደራጀና በተቀናጀ መልኩ እየሰራ ስለመሆኑ አንስተዋል።

የቁሳቁስ ስርጭቱ በጥንቃቄና ደህንነቱ በተጠበቀ መልኩ በጸጥታ ሃይል ታጅቦ እየተጓጓዘ ወደ ምርጫ ጣቢያዎች ተደራሽ እየሆነ እንደሚገኝ ኢዜአ ዘግቧል።

በክልሉ በ3 ምርጫ ክልሎች 296 የምርጫ ጣቢያዎች የፊታችን ሰኞ ድምጽ የሚሰጥ መሆኑን ገልጸው፥ዜጎች የወሰዱትን ካርድ ዋጋ በመስጠት እንዲወስኑበት መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review