AMN-ግንቦት 25/2018 ዓ.ም
ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ መራጩ ሕዝብ ለዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ያለውን ቁርጠኝነትና ፍላጎት በተግባር ያረጋገጠበት መሆኑን የአዲስ አበባ ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ገለጸ።
የአዲስ አበባ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ትናንት ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም የተከናወነውን የ7ኛውን ጠቅላላ ምርጫ የድምፅ አሰጣጥ ሂደት መጠናቀቅ አስመልክቶ ዛሬ ይፋዊ መግለጫ ሰጥቷል።
7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ከቅድመ ዝግጅቱ ጀምሮ ግልጽነት እና ፍትሃዊነትን በአዲስ አበባ ደረጃ አሻግሮ ማሳየት የቻለ፣ በመራጩ የከተማዋ ህዝብ ብቻ ሳይሆን በተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎችም ቅቡልነት ያሳየ መሆኑን የጋራ ም/ቤት አስታውቋል፡፡
ምክር ቤቱ የምርጫውን መጠናቀቅ አስመልክቶ መግለጫ ሰጥቷል፤የመግለጫው ሙሉ መልዕክት እንደሚከተለው ቀርቧል።
ውድ የከተማችን ነዋሪዎች እንዲሁም በዚህ የከተማ አስተዳደር ምርጫ የተሳተፋችሁ መራጮች፤ 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ከቅድመ ዝግጅቱ ጀምሮ ግልጽነት እና ፍትሃዊነትን በአዲስ አበባ ደረጃ አሻግሮ ማሳየት የቻለ፣ በመራጩ የከተማዋ ህዝብ ብቻ ሳይሆን በተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎችም ቅቡልነት ያሳየ ነው፡፡
መንግስት በከተማችን የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ላይ ያለውን ቁርጠኝነት በተግባር ያሳየበትና በዚህም የኢትዮጵያ አሸናፊነት የተረጋገጠበት ሌላኛው ታሪካዊ ምዕራፍም ነበር።

የአዲስ አበባ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ከብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የከተማዋ ቅርንጫፍ ጋር በቅርብ ትብብር በመስራት የዕጩዎች ምዝገባን፣ የሎጀስቲክስ አቅርቦትንና የተወዳዳሪዎችን ዝግጅት በከፍተኛ ጥንቃቄ እና በልዩ ትኩረት ሲከታተል ቆይቷል::
በዚህ ረገድ በከተማዋ የተከናወኑ ተግባራት ለምርጫው ፍጹም ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ለመሆኑ መሰረት ጥሏል፡፡
ከነዚህ መሀከል አንዱ የዲጂታል ዕጩዎች ምዝገባ ሂደት፡- በዚህ ምርጫ ውስጥ እንደ ትልቅ ጅማሮ የሚወሰድ ሲሆን፣ ይህ ዘመናዊ አሰራር በከተማችን የምርጫ ክልሎች አላስፈላጊ መጉላላትን የቀነሰ የዕጩዎችን መረጃ ጥራትና ደህንንት ያረጋገጠ አንዲሁም የአሰራር ግልጽነትን የፈጠረ ነበር።
በተለይ ትናንት ግንቦት 24/2018 ዓ.ም መላው የከተማችን አዲስ አበባ ነዋሪዎች የነገዋን የመዲናችንንና ሀገራችን እጣ ፈንታ ለመወሰን እና የሀገራችንን ዴሞክራሲያዊነት ይበልጥ ለማጠናከር ካርድ ያወጣ መራጭ ሁሉ ከማለዳው 12፡00 ሰዓት ጀምሮ ያለ ምንም ቀስቃሽ በነቂስ በመውጣት እምነት ለጣለበት ፓርቲ ድምጹን ሰጥቷል።
ሂደቱም እጅግ የተረጋጋ፣ የስለጠነና የከተማችንን መጻኢ የዴሞክራሲ ስርዓት ትግበራ ሂደት ያጠናከረ ሆኖ አልፏል፡፡
በተለይም ሴቶች፣ ወጣቶችና አረጋውያን ያሳዩት ከፍተኛ ተሳትፎ የምርጫውን ሂደት ይበልጥ አድምቆታል:: በመላው አዲስ አበባ ከተማ ህዝብ እርስ በእርሱ እየተጋገዘ፣ ለደካሞችና ለአካል ጉዳተኞች ቅድሚያ እየሰጠ፤ ፍጹም በሆነ የከተማ ጨዋነትና ፍቅር ምርጫውን አከናውኗል፡፡
በሂደቱም በከተማዋ ምንም አይነት የጸጥታ መደፍረስም ሆነ የምርጫ ህግ መጣስ ሳይኖር፣ ፍጹም ሰላማዊ ሆኖ መጠናቀቁ የከተማችንን ነዋሪዎችና የከተማዋን የጸጥታ አካላት ከፍተኛ የብስለት ደረጃ የሚያሳይ ነው::
ይህ ታላቅ የሰላም ድባብ አዲስ አበባ ሞዴል የዴሞክራሲ ስርዓት መገንባት እንደምትችል በተግባር ያስመሰከረችበት ደማቅ አጋጣሚም ሆኗል፡፡

በተለይ ከከተማ አቀፍ ሚዲያ አጠቃቀም ጋር ተያይዞ የአየር ሰዓት ክፍፍል እና ፍትሀዊነት በከተማ አስተዳደሩ የብዙሃን መገናኛዎች የተመደበው ነጻ የአየር ሰዓት አጠቃቀም እጅግ ፍትሃዊ፣ ግልጽ እና ሁሉንም ፓርቲዎች ያስተናገደ ነበር፡፡
እያንዳንዱ የፖለቲካ ፓርቲ የራሱን መርሃ ግብርና የከተማዋን መሻሻል የሚያሳይ የፖሊሲ አቅጣጫ ያለምንም ገደብና ጫና ለህዝብ ያቀረበበት ነጻና ገለልተኛ ምዕራፍ ተፈጥሯል፤ ይህ ታሪካዊ የአየር ሰዓት አጠቃቀም በከተማችን የነጻ መገናኛ ብዙሃን ባህልን ለማሳደግና ለወደፊቱ መልካም አርአያ ለመሆን የቻለ ተግባር ነው፡፡
በሌላ በኩልም የፖሊሲ አማራጮች አቀራረብ መድረክ የሀሳብ ፍልሚያ እንጂ የጥልና የትግል መድረክ አለመሆኑን በተግባር የታየበት፣ የፓርቲዎቻችንን የፖለቲካ ብስለት ደረጃ ከፍ ማለቱን የታየበት ነው።
እነዚህ መድረኮች በከተማችን አዲስ አበባ ያሉ ዜጎች የፓርቲዎችን ዝግጁነትና ብቃት እንዲመዝኑ ትልቅ አጋጣሚ ፈጥረዋል፡፡ የተፈጠረውን ምቹ ሁኔታ በመጠቀም እያንዳንዱ ፓርቲ የራሱን ህዝባዊ ራዕይ በፍትሃዊነትና በነጻነት ለከተማዋ ህዝብ አስተዋውቋል።
በአዲስ አበባ ከሚገኙ የክፍለ ከተማና የወረዳ ምርጫ ጣቢያዎች የሚመጡ ጥቆማዎችንና የአሰራር ችግሮችን በጋራ በመገምገም፣ ከምርጫ ቦርድ የከተማዋ አመራሮች ጋር በቀጥታ በመነጋገር አፋጣኝ የእርምት እርምጃዎች እንዲወስዱ አድርጓል፡፡
ይህ አይነቱ ተቋማዊ ቅንጅት የምርጫውን ተአማኒነት ከመጨመሩም በላይ፣ በፓርቲዎችና በአስፈጻሚው አካል መካከል የመተማመን መንፈስ እንዲገነባ አድርጓል፡፡
ሌላው የከተማችን የጸጥታ አካላት ያከናወኑት ተግባር ሊመሰገን የሚገባው ነው፡፡ ያለምንም ወገንተኝነት፣ ፍጹም ገለልተኛና ፕሮፌሽናል በሆነ መንገድ የአዲስ አበባ የምርጫ ጣቢያዎችንና የመራጩን ህዝብ ደህንነት ሲጠብቁ ውለዋል።
የጸጥታ አካላቱ የሰሩት ስራ ህዝቡ በነጻነትና በደህንነት ስሜት ወጥቶ ድምጹን እንዲሰጥ ትልቁን ሚና ተጫውቷል። አሁን በከተማችን የምርጫው እለት ሂደትና የድምፅ መስጠት ተግባር በስኬት ተጠናቋል፡፡ ወደ ቀጣዩና ወሳኙ ምዕራፍ እየተሸጋገረ ይገኛል፡፡
በዚህ ወቅት መላው የከተማችን ነዋሪዎች፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች አባላትና ደጋፊዎች ፍጹም የሆነ ትዕግስትን ሊያሳዩ ይገባል። የድምጽ ቆጠራውና ውጤቱን የማደራጀት ስራ በምርጫ ቦርድ ህጋዊ አሰራር መሰረት በጥንቃቄ የሚከናወን በመሆኑ፣ በከተማ ደረጃ ያለው ውጤት በኦፊሴላዊ መልኩ እስኪገለጽ ድረስ በትዕግስት እንዲጠብቅ ምክር ቤታችን ጥሪውን ያቀርባል::
ማንኛውም ወገን የከተማዋን ምርጫ ውጤት ፍጹም በሆነ ሰላማዊ መንገድና በፀጋ የመቀበል ታሪካዊና ሞራላዊ ግዴታ አለበት:: ቅሬታዎች ቢኖሩ እንኳ በህጋዊና በሰላማዊ መንገድ ማቅረብ ተገቢ መሆኑን እናሳስባለን፡፡
ያሸነፈው ይህ ምርጫ የኢትዮጵያና አዲስ አበባ አሽናፊነት የሚረጋገጥበት በመሆኑ ፣ ያላሸነፉት ደግሞ እንደ መልካም ተፎካካሪ ሆነው የከተማዋን የዴሞክራሲ ጉዞ ፓርቲ የከተማዋን ህዝብ በቅንነትና በታማኝነት እንዲያገለግል እንዲያጠናክሩ የጋራ ምክር ቤቱ ያምናል:: ውጤቱን በፀጋ መቀበል የሽንፈት ሳይሆን የታላቅ የፖለቲካ ብስለትና ለከተማዋ የመቆርቆር ማሳያ ነው::
በመጨረሻም ይህ 7ኛው የከተማ አስተዳደር ምርጫ አዲስ አበባ ወደ ላቀ የዴሞክራሲ ስርዓትና ልዕልና የምታደርገውን ጉዞ እንደ ሀገር በጠንካራ መሰረት ላይ ያቆመ ታሪካዊ ሁነት ነው፡፡ በዚህም መራጩ ህዝብ እንደተለመደው ለከተማዋ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ያለውን ጽኑ ቁርጠኝነትና ፍላጎት በተግባር አረጋግጧል::
በዚሁ አጋጣሚ የአዲስ አበባ ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ለዚህ ምርጫ ስኬት ላበረከቱ አካላት፣ ለመላው መራጭ ህዝባችን፣ ለብሄራዊ ምርጫ ቦርድ የከተማዋ አመራሮችና ሰራተኞች፣ ለከተማዋ የጸጥታ አካላት እንዲሁም ለመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች የላቀ ምስጋናውን ያቀርባል፡፡
በአንዋር አህመድ