AMN ሰኔ 1/2018
የሰው ኃይል ልማትን ከቴክኖሎጂ ጋር በማሰናሰል በአገልግሎት ዘርፉ የሚታዩ ችግሮችን ለመፍታት በተሰራዉ ስራ አመርቂ ውጤት መምጣቱን የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ አቶ ጃንጥራር አባይ ገለጹ።
የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባና የኢንደስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ጃንጥራር አባይ የአዲስ መሶብ የአንድ ማዕከል ዲጂታል የመንግስት አገልግሎት የካ ማዕከልን አገልግሎት አስጀምረዋል።
አቶ ጃንጥራር በወቅቱ ባደረጉት ንግግር በአገልግሎት አሰጣጥ ዘርፉ ስር የሰደዱ ችግሮችን ለመፍታት የተለያዩ አሰራሮች ቢዘረጉም ለህብረተሰቡ ጥያቄ ምላሽ ማምጣት አልተቻለም ብለዋል።
ይሁን እንጂ የሰው ኃይል ልማትን ቴክኖሎጂን ጋር አሰናስሎ ገቢራዊ በተደረገው የመሶብ የአንድ ማእከል ዲጂታል የመንግስት አገልግሎት በመስኩ የሚታዩ ችግሮችን በመፍታት በኩል ተጨባጭ ውጤቶችን አምጥቷል ብለዋል።

እንደ ከተማ አስተዳደሩም ይህንኑ ታሳቢ በማድረግ ባለፉት ዘጠኝ ወራት በ9 ክፍለ ከተሞች የመሶብ ማዕከላትን ተደራሽ ማድረግ ተችሏል ያሉት አቶ ጃንጥራር በተያዘው ወር በቀሪ ሁለት ክፍለ ከተሞች የተገነቡትን አገልግሎት እንዲጀምሩ ይደረጋል ብለዋል።
ማእከላቱን ተደራሽ ከማድረግ ባሻገርም ተጨማሪ ተቋማትንና የአገልግሎት አይነቶችን ወደ ማእከላቱ የማስገባት ስራ ይከናወናል ብለዋል።
በማእከሉ 22 ተቋማት 114 አገልግሎቶችን በ96 መስኮትቶች አገልገሎት የሚጥ መሆኑ ተመላክቷል።
በሄኖክ ዘነበ