AMN- ሰኔ 01/2018 ዓ.ም
7ኛው ጠቅላላ ምርጫ በኢትዮጵያ ጠንካራ ሐገረ መንግሥት እንዲፀና የሚያስችል ሕዝባዊ ቅቡልነት የሚፈጥር መሆኑን የሕግ አማካሪና ጠበቃው ኪያ ፀጋዬ ተናገሩ።
ከኤ ኤም ኤን ሰንኮፍ የቴሌቪዥን መሰናዶ ጋር ቆይታ ያደረጉት የሕግ አማካሪና ጠበቃው ኪያ ፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ በምርጫ ብቻ መንግሥት መቋቋም እንዳለበት ግልጽ መልዕክት ማስተላለፉን አብራርተዋል።

ሕዝቡ ዲሞክራሲያዊ መብቱን እንዳያካሂድ በርካታ ማጠልሸቶች ሲካሄድ ቢቆይም ፣ ጫናዎቹን በመቋቋም ድምፅ በመስጠት ብልህነቱን አሳይቷል ብለዋል።
በሕዝብ የተመረጠ ጠንካራ መንግሥት መኖር እጅግ ወሳኝ መሆኑን አርቆ ያስተዋለው የኢትዮጵያ ሕዝብ ፣ ሕጋዊ መንግሥት ብቻ ማስተዳደር እንዳለበት ውሳኔውን ገልጿል ብለዋል።
የሕግ ምሁሩ ኪያ ከማናቸውም ጊዜ በላይ የኢትዮጵያ ሰላምና ደሕንነት የሚያስፈልግበት ጊዜ መሆኑን አፅንኦት ሰጥተዋል።
ምርጫው በአፍሪካ ቀንድ ጠንካራ እና በሕዝብ ቅቡልነት የጸና የኢትዮጵያ መንግሥት እንዲኖር በማስቻል ሚናው የጎላ መሆኑን ነው የሕግ አማካሪና ጠበቃው ያብራሩት።

ሕዝብ ይሁንታ የሰጠው መንግሥት በመስከረም ስልጣኑን መረከቡም ፣ ኢትዮጵያን ወክሎ ብሔራዊ ጥቅሟን የሚያስጠበቁ ሥራዎችን በሙሉ እምነት እንዲያከናውን የሚያስችል መሆኑን ነው የጠቀሱት።
ምርጫው በስኬት መጠናቀቁም የሕዝብ ቅቡልነት ያለው መንግሥት እንዳይመሠረት ሲሸርቡ የነበሩ ኃይሎችን ፍላጉትም አምክኗል ብለዋል።

ተመራጩ መንግሥት እስከ ሌሊት ቆሞ ወረፋ ጠብቆ ድምፅ የሰጠው ሕዝብ ከፍተኛ አደራ እንዳለበት የሕግ አማካሪና ጠበቃው የአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ መምህር ኪያ ፀጋዬ ተናግረዋል።
የሕዝብ ድምፅ ያገኘው መንግሥትም ፣ ሐገራዊ መግባባትን የሚፈጥሩ ስራዎችን በማከናወን ፣ የሕዝብ ጥያቄዎችን ምላሽ እንዲያገኙ ማድረግ እንዳለበት ገልፀዋል።
በታደሰ ሽፈራው