AMN – ሰኔ 15/2018 ዓ.ም

የ2018 ዓ.ም የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር “ተስፋን እንትከል” በሚል መሪ ቃል ትናንት በይፋ ተጀምሯል።
በማስጀመሪያ ሥነ ሥርዓቱ ላይ የተገኙት የከተማ ውበትና አረንጓዴ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ግርማ ሰይፉ እንደገለጹት፤ የአረንጓዴ አሻራ ንቅናቄ ለዛሬ ጊዜያዊ ጥቅም ብቻ የሚከናወን ሳይሆን ለልጅ ልጆች የሚተላለፍ ዘላቂ የሕይወት ዋስትና ነው።
ይህ ታላቅ የችግኝ ተከላ ተግባር መጪው ትውልድ ልክ እንደ አድዋ ድል በጀግንነት ታሪክ የሚተርከው ታላቅ ሀገራዊና ትውልዳዊ ገድል መሆኑንም አብራርተዋል።

የአረንጓዴ አሻራ ንቅናቄ ከቁጥሩና ከደን ሽፋኑ ዕድገት በላይ ያመጣው ትልቁ ውጤት የማኅበረሰቡን አስተሳሰብ መለወጥ መቻሉ እንደሆነ የጠቆሙት ኃላፊው፣ በዚህ የአረንጓዴ ልማትና ውበት ሥራ አማካኝነት አዲስ አበባ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ እውቅና እንድታገኝ ማስቻሉን ገልጸዋል።

ከተማዋ በአሁኑ ወቅት በአፍሪካ ደረጃ በምሳሌነት የምትጠቀስ ማራኪ ከተማ እየሆነች እንደምትገኝም አክለው ገልጸዋል።
አቶ ግርማ አክለውም ባለፉት ሰባት ዓመታት በከተማዋ 90 ሚሊዮን ችግኞችን በመትከል፣ የአረንጓዴ ሽፋኑን እጅግ ዝቅተኛ ከነበረበት 2 ነጥብ 8 በመቶ ወደ 24 በመቶ ማድረስ መቻሉን አብራርተዋል።

ከተማዋን በልማት ዕቅዱ በተቀመጠው መሠረት 30 በመቶ በአረንጓዴ የመሸፈን ግብ በአጭር ጊዜ አሳክቶ፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ አዲስ አበባን ዘመናዊ፣ ውብና ምቹ ከተማ የማድረግ ዕቅዱ አሁን ላይ በጽኑ መሠረት ላይ እንደሚገኝም አስገንዝበዋል።
ይህንን ትልቅ ስኬት እውን ለማድረግ የመንግሥት የፖለቲካ ቁርጠኝነት እና የሕዝብ ንቁ ተሳትፎ ወሳኝ ግብዓቶች መሆናቸውን የጠቀሱት ኃላፊው፣ ነዋሪዎች ችግኝ ለመትከል ካላቸው ከፍተኛ ተነሳሽነት ባሻገር፣ ከተተከለ በኋላ ለችግኞቹ የሚያደርጉት ጥበቃና እንክብካቤ እጅግ አስደማሚና ልብን የሚያሞቅ መሆኑን በምሳሌነት አንስተዋል።
በመጨረሻም እያንዳንዱ የከተማዋ ነዋሪ የጀመረውን አርዓያነት ያለው ተግባር አጠናክሮ በመቀጠል፣ ከመኖሪያ ቤቱ ጀምሮ መንደሩንና አካባቢውን በአረንጓዴ ተክሎች እንዲሸፍን ጥሪ አቅርበዋል።
በረከት ጌታቸው