የኢትዮጵያ ጠንካራ ፖለቲካል ኢኮኖሚ አቅም የቀጠናው (የምስራቅ አፍሪካ) ዋስትና !

You are currently viewing የኢትዮጵያ ጠንካራ ፖለቲካል ኢኮኖሚ አቅም የቀጠናው (የምስራቅ አፍሪካ) ዋስትና !

ምስራቅ አፍሪካ በጂኦፖለቲካዊ አቀማመጡና በተለዋዋጭ ባህሪው በዓለም አቀፍ መድረክ ከፍተኛ ትኩረት የሚሻ ቀጠና ነው። በዚህ ስትራቴጂካዊ ቀጠና ውስጥ የኢትዮጵያ ሚና ተራ ተመልካችነት ሳይሆን የቀጠናው የሰላምና የልማት ምሰሶነት ሚና ነው። “የኢትዮጵያ ጠንካራ ፖለቲካል ኢኮኖሚ አቅም የቀጠናው ዋስትና ነው” የሚለው አገላለፅ ወቅታዊ ሀገራዊ እውነታንና ቀጠናዊ አስፈላጊነትን በትክክል የሚያንጸባርቅ ሲሆን፣ የሀገሪቱ የውስጥ ጥንካሬ ለጎረቤቶቿም የሚተርፍ የደህንነትና የብልጽግና ጋሻ መሆኑን ያበስራል።

ኢትዮጵያ ታሪክ የማይረሳው የታላቅነት፣ የግዙፍነት እና የጽናት ተምሳሌት የሆነ ህዝብ የኖረባትና የሚኖርባት ታላቅ ሀገር ናት። ህዝቧ ፈታኝ ታሪካዊና ወቅታዊ ውጣ ውረዶችን በጽናት በማሸነፍ፣ ሀገራዊ አንድነቱንና ሉዓላዊነቱን አስከብሮ የማሻገር ተፈጥሯዊ ጥበብ አለው። ይህ በማንኛውም አጋጣሚ የማይበገር ማህበራዊ መሰረት፣ የሀገሪቱን የፖለቲካ ኢኮኖሚ መዋቅር የሚደግፍ ዋናው የሀይል ምንጭ ሲሆን፣ ለቀጠናው መረጋጋትም የማይናወጥ ዘላቂ መሰረት ጥሏል።

ዛሬ ኢትዮጵያ የጠንካራና እያደገ የመጣ ኢኮኖሚ ባለቤት ለመሆን በምታደርገው ጉዞ መጠነ-ሰፊ የሆኑ የፖሊሲና የመዋቅር ማሻሻያዎችን እያከናወነች ትገኛለች። የግብርናው ዘርፍ ምርታማነት ማደግ፣ የኢንዱስትሪ መናኸሪያዎች መስፋፋትና የዲጂታል ኢኮኖሚው መነቃቃት ሀገሪቱን የቀጠናው የኢኮኖሚ ማዕከል እያደረጋት ይገኛል። ይህ ጠንካራ የኢኮኖሚ አቅም የውስጥ ፍላጎትን ከመሸፈን ባለፈ፣ የቀጠናዊ ትስስርን በማጠናከር ለምስራቅ አፍሪካ ሀገራት ሰፊ የገበያና የኢንቨስትመንት እድል እየፈጠረ ይገኛል።

የሀገሪቱ የፖለቲካ ኢኮኖሚ ስትራቴጂ መሰረት ያደረገው መሰረተ-ልማትን በማስፋፋት ላይ ነው። የሀይል ማመንጫ ግዙፍ ፕሮጀክቶች፣ የባቡርና የመንገድ ትስስሮች እንዲሁም የሎጂስቲክስ ማሻሻያዎች የኢትዮጵያን የውስጥ ኢኮኖሚ ከቀጠናው ጋር እያቆራኙት ነው። ኢትዮጵያ ለጎረቤት ሀገራት የምታቀርበው የኤሌክትሪክ ሀይልና የምታከናውነው የድንበር ተሻጋሪ ንግድ እንቅስቃሴ፣ የፖለቲካ ኢኮኖሚ አቅሟ በቀጥታ የቀጠናው የጋራ ብልጽግና ዋስትና መሆኑን በተግባር ያሳያል።

ከኢኮኖሚ ጥንካሬው ጎን ለጎን፣ በሀገሪቱ እየተከናወነ ያለው የፀና ዴሞክራቲክ ስርዓት ግንባታ ሂደት ለዘላቂ ሰላም ዋነኛው ምሰሶ ነው። ተቋማዊ ሪፎርሞች፣ የፍትህ ስርዓቱ ገለልተኝነት እና የህዝብ ተሳትፎን ማጎልበት የሀገር ውስጥ የፖለቲካ ምህዳሩን እያሰፉት ይገኛሉ። የውስጥ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት መፅናት ሀገራዊ አንድነትን እና ስምምነትን ከመፍጠሩም በላይ፣ በግጭትና አለመረጋጋት ለሚታወቀው የምስራቅ አፍሪካ ቀጠና መልካም ተሞክሮና የሰላም ተምሳሌት መሆን ችሏል።

የሀገር ሉዓላዊነትና የቀጠናው ሰላም ያለ አስተማማኝ የመከላከያ ሀይል ሊታሰብ አይችልም። ኢትዮጵያ ለዚህ አስተማማኝ ምላሽ የሚሰጥ፣ በቴክኖሎጂና በስልጠና የዳበረ ብቁና ጠንካራ መከላከያ የገነባች ሀገር ናት። ይህ የሀገር መከላከያ ሰራዊት የሀገሪቱን ድንበር ከማስከበር ባለፈ፣ በተለያዩ የአፍሪካ ህብረትና የተባበሩት መንግስታት የሰላም ማስከበር ተልዕኮዎች ላይ በማሳየት ላይ ያለው ብቃትና መስዋዕትነት ምስራቅ አፍሪካን ከሽብርተኝነትና ከአክራሪነት ስጋት የታደገ ታላቅ ሀይል ነው።

ይህም የኢትዮጵያ የውስጥ ጥንካሬ በቀጥታ ከቀጠናው ህልውና ጋር የተሳሰረ ያደርገዋል። ኢትዮጵያ የፖለቲካ ኢኮኖሚ አቅሟ ሲያድግ፣ መከላከያዋ ሲጠነክርና ዴሞክራሲያዊ ተቋሞቿ ሲፀኑ የምስራቅ አፍሪካ ቀጠና ይበልጥ አስተማማኝና ስጋት የሌለበት ይሆናል። በተቃራኒው የኢትዮጵያ መዳከም የቀጠናውን ሚዛን የሚያናጋ በመሆኑ፣ የሀገሪቱ ሁለንተናዊ አቅም መጎልበት ለምስራቅ አፍሪካ ሀገራት የተረጋጋ የፖለቲካ ምህዳርና የኢኮኖሚ ዋስትና ሆኖ ያገለግላል።

በጥቅሉ ኢትዮጵያ በታሪኳና በማንነቷ የግዙፍና የጽናት ተምሳሌት ህዝብ ሀገር መሆኗን በተግባር ያረጋገጠች፣ የጠንካራ ኢኮኖሚ ባለቤት፣ የፀና ዴሞክራቲክ ስርዓት ግንባታን እያረጋገጠች ያለችና ብቁ መከላከያ የገነባች ሀያል ሀገር ናት። ይህ ሁለንተናዊ የፖለቲካ ኢኮኖሚ አቅም የራሷን ብልጽግና ከማረጋገጥ ባለፈ፣ ለምስራቅ አፍሪካ ቀጠና ዘላቂ ሰላም፣ ልማትና መረጋጋት የማይተካ ትልቁ ዋስትና ሆኖ ይቀጥላል።

በሹመት ደመቀ

#Ethiopia

#beautifuladdis

#Ethiopiarisings

#Eastaffairs

See less

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review