AMN – ሰኔ 30/2018 ዓ.ም
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት የሚፈታተን ማንኛውም ዓይነት ኃይል ቢመጣ፣ መንግሥት የሀገሪቱን ደህንነትና ሉዓላዊነት ለመጠበቅ ከየትኛውም ጊዜ በበለጠ ሙሉ ዝግጁነት እንዳለው አስታወቁ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህንን ያሉት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 30ኛ መደበኛ ጉባኤ ላይ ተገኝተው፣ ከምክር ቤቱ አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት ነው፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ መንግሥት የሕዝብን ሰላም ለማስከበር ትዕግሥት በተሞላበት መንገድ መሥራቱን እንደሚቀጥልና የሀገሪቱን ሉዓላዊነት ለመድፈር የሚመጣን ማንኛውንም ኃይል ለመመከት ግን ከመቼውም ጊዜ በላይ በቁርጠኝነት መዘጋጀቱን አረጋግጠዋል።

የፕሪቶሪያውን የሰላም ስምምነት ተከትሎ በትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር መቋቋሙን ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚህም ከ60 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ታጣቂዎች አስፈላጊው ድጋፍ መደረጉንና ታጣቂዎቹን ትጥቅ የማስፈታት፣ የመልሶ ማቋቋም እና ወደ ማኅበረሰቡ የመቀላቀል ሥራ በስኬት መከናወኑን ገልፀዋል፡፡
ስምምነቱ ለትግራይ ሕዝብ ትልቅ እፎይታን ሰጥቷል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ በአሁኑ ወቅት በትግራይ ክልል ሰላምን እያወኩ ያሉት ጥቅመኛ ኃይሎች መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡
የትግራይ ክልል መውደም አለበት ብለው የሚያምኑ ኃይሎች ከፕሪቶሪያው ስምምነት በኋላ ማኩረፋቸውን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ በአክራሪ ኃይሎች አማካኝነት በየቀኑ አዲስ ጦርነት ሊቀሰቅሱ የሚችሉ ትንኮሳዎች እየተፈጸሙ መሆኑን አስታውቀዋል።
የትግራይ ሕዝብ የችግሩ ባለቤት ሳይሆን የችግሩ ገፈት ቀማሽ መሆኑን በመጥቀስ ፣ በአሁኑ ወቅት በትግራይ ክልል ውስጥ ከሚኖረው ሕዝብ ይልቅ በሌሎች የኢትዮጵያ ክፍሎች የሚኖሩ የትግራይ ተወላጆች ይበልጥ በሰላም፣ በነፃነትና በደህንነት ሕይወታቸውን እየመሩ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
በታምራት ቢሻው