የቡልቡላ ፓርክ ለውጥ፡ ከአቧራማ ሜዳ እስከ ዘመናዊ የስፖርትና የመዝናኛ ስፍራ

You are currently viewing የቡልቡላ ፓርክ ለውጥ፡ ከአቧራማ ሜዳ እስከ ዘመናዊ የስፖርትና የመዝናኛ ስፍራ

AMN- ነሐሴ 18/2018 ዓ.ም

አዲስ አበባ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ለአካባቢው ነዋሪዎች ስጋት የነበሩ ቦታዎችን የተፈጥሮ ይዞታቸውን ጠብቆ በማልማት ለትውልድ ማረፊያነት ማዋሏ ይታወቃል።

ከእነዚህም መካከል አንዱ የሆነው የቡልቡላ ፓርክ በአዲስ አበባ ነዋሪዎች ዘንድ ከፍተኛ አድናቆትን እያተረፈ ይገኛል።

ከዚህ ቀደም ደህንነቱና ንጽህናው ያልተጠበቀ ጫካ እና የአውሬ መኖሪያ የነበረው ይህ ስፍራ፣ ዛሬ ላይ ወላጆች ልጆቻቸውን ይዘው የሚዝናኑበት ውብ ማረፊያ መሆኑ በፓርኩ የተከናወኑት ማሻሻያዎች በአካባቢው ማህበረሰብ ሕይወት ላይ ካመጡት ለውጥ መካከል ተጠቃሽ ነው።

ህጻናት እንዲዝናኑ፣ አእምሮአቸውን እንዲያድሱ እና በቀጣይ ቀናት ትምህርታቸው ላይ እንዲያተኩሩ ትልቅ እገዛ አድርጓል።

ከዚህ ቀደም አቧራማና ለጤና አስጊ በነበሩ ሜዳዎች ላይ ይለማመዱ የነበሩ ታዳጊዎች አሁን ላይ በተስተካከለ ስፍራ ስፖርት በመስራታቸው ደስተኞች መሆናቸውን ለኤ ኤም ኤን ገልጸዋል።

የአዲስ አበባ ነዋሪ የሆኑት አቶ ህንጻ መሰለ ስለ ሥፍራው ሲገልጹ፣ ከዚህ በፊት አውሬና ጫካ የነበረበት ቦታ እንደነበርና ዛሬ ግን አዋቂዎችና ልጆች መጥተው የሚዝናኑበት ድንቅ ቦታ ሆኗል ብለዋል።

መንግስት በዚህ ላይ ትኩረት አድርጎ መስራቱ በጣም ትልቅ ነገር መሆኑንም ነው ያነሱት።

ልጆችን ከዚህ በፊት ማጫወት አስቸጋሪ እንደነበር የሚናገሩት ደግሞ ሌላኛው የአዲስ አበባ ነዋሪ አቶ ኢብራሂም አህመድ፣ ከጠበቁት በላይ አዋቂዎችንና ልጆችን የሚያዝናና በጣም የሚያምር ቦታ ሆኖ እንዳገኙት በመግለፅ፣ ደስተኞች መሆናቸውንም ተናግረዋል፡፡

የ ፒኬ ኤስ ስፖርት ቡድን ሰልጣኞች ዮናዳብ ግዛው እና ያፌት ስንታየሁ በበኩላቸው፣ ከዚህ ቀደም ልምምድ የሚያደርጉበት ሜዳ ጭቃና አቧራ የነበረና ለበሽታ እንደሚያጋልጥ በማንሳት፣ አሁን ግን በተሻለ መልኩ በመሰራቱ ለጤናም ሆነ ለትምህርታቸው እንደሚጠቅም ገልጸዋል፡፡

ወደፊትም ሀገራቸውን በኳስ ማስጠራት እንደሚፈልጉ ነው የተናገሩት።

በፍሬሕይወት ብርሃኑ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review