AMN – ጥቅምት 19/2019 ዓ.ም
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በሶስተኛው የሩሲያ-አፍሪካ ጉባኤ ባደረጉት ንግግር ኢትዮጵያ በሰው ሠራሽ አስተውሎት ዘርፍ ያላትን ራዕይ በማስረዳት ከሩሲያ ዩኒቨርሲቲዎችና የምርምር ተቋማት ጋር በትምህርትና በምርምር መስኮች የጋራ ትብብር እንዲደረግ ጥሪ አቅርበዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በንግግራቸው፤ የቴክኖሎጂ ትብብር መሠረተ ልማቶችን ከመገንባት ባለፈ፣ እነዚህን ሥርዓቶች ማስተዳደር፣ ማስኬድና መቆጣጠር የሚችሉ የሀገር ውስጥ ባለሙያዎችን ማፍራት እንዳለበት አስገንዝበዋል።
በዘመናችን የእውቀትና የቴክኖሎጂ አቅም ማለት በከፍተኛ ደረጃ ከሰው ሠራሽ አስተውሎት ጋር የተያያዘ መሆኑን ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የኤአይ ቴክኖሎጂዎች አሁን ባለው መንገድ መገንባታቸው የትኞቹ ቋንቋዎች በቴክኖሎጂው እንደሚወከሉና የማን ማንነትና ተሞክሮ እንደሚካተት እንደሚወስን ገልጸዋል።
አንድ አፍሪካዊ ተመራማሪ በሕዝባችን ቋንቋ የኤአይ መፍትሔዎችን መፍጠር መቻል አለበት ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፣ ተቋሞቻችንም እነዚህ መፍትሄዎች የእኛን መረጃ እንዴት እንደሚጠቀሙ መወሰን አለባቸው ሲሉ አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
ኢትዮጵያ የመደመር የሰው ሠራሽ አስተውሎት ዩኒቨርሲቲ እያቋቋመች መሆኑን ያስታወቁት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) የሩሲያ ዩኒቨርሲቲዎችና ተቋማት በማስተማርና በምርምር ከኢትዮጵያ ጋር እንዲሠሩ ጋብዘዋል።
እውቀት አሁን ወደ ሁለቱም አቅጣጫ እየተንቀሳቀሰ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ከ130 ዓመታት በፊት የሩሲያ ሕክምና መጽሐፍ ወደ አማርኛ ከተረጎመ በኋላ፣ ዘንድሮ ደግሞ የመደመር መጽሐፍ ወደ ሩሲያኛ መተርጎሙን በማንሳት የሁለቱ ሀገራት ትብብርን አስፈላጊነት አስረድተዋል።
በታደሰ ሽፈራው