AMN – ጥቅምት 20/2019 ዓ.ም
በኢትዮጵያና በሩሲያ ፌዴሬሽን መካከል ያለው ታሪካዊና ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት፤ ብሔራዊ ጥቅምን በሚያስከብር፣ የሁለትዮሽ ትብብርን በሚያጠናክር እና ስልታዊ አጋርነትን ወደ ላቀ ደረጃ በሚያሸጋግር መልኩ እየጎለበተ ይገኛል።
ሁለቱ ሀገራት ከአንድ ክፍለ ዘመን በላይ ያስቆጠረ፣ በመከባበርና በጋራ ተጠቃሚነት ላይ የተመሰረተ ጠንካራ ወዳጅነት አላቸው።
ይህንን ዘላቂ ግንኙነት የበለጠ ለማጠናከር በሞስኮ ከተካሄደው 3ኛው የሩሲያ-አፍሪካ ጉባኤ ጎን ለጎን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እና የሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ያደረጉት የሁለትዮሽ ውይይት ወሳኝ ምዕራፍ ከፍቷል።
መሪዎቹ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን የቆየ ግንኙነት ይበልጥ ማጠናከር በሚቻልባቸው መንገዶች ዙሪያ ፍሬያማ ውይይት አድርገዋል።
በዚህም የኒውክሊየር ኃይል ልማት፣ የጤና፣ የንግድ እንዲሁም በጋራ ፍላጎት ላይ የተመሰረቱ የሁለትዮሽና የባለብዙ ወገን ጉዳዮች ላይ መክረዋል።
ከዲፕሎማሲያዊና ኢኮኖሚያዊ ትብብሮች ባለፈ በኢትዮጵያ እና በሩሲያ መካከል ያለው አጋርነት ተጨባጭ ፍሬዎችን እያፈራ ይገኛል።
በዚህም መሰረት ሁለቱ ሀገራት የኒውክሊየር ኃይል ማመንጫ በጋራ ለመገንባት በቁርጠኝነት እየሠሩ ነው።
በ3ኛው የሩሲያ-አፍሪካ ጉባኤ ወቅትም ኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም ከሩሲያ መንግሥት ጋር በደረሰችው ስምምነት መሠረት፣ የመጀመሪያዎቹን 12 ዘመናዊ የሱ-35 (Su-35 4++ Generation) የጦር ጄቶች ርክክብ ፈጽማለች።
በተጨማሪም ሀገሪቱ አራት የኤስ-400 (S-400) የአየር መከላከያ ሥርዓት ባትሪዎችን ትረከባለች።
የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ዘመናዊነትና ዝግጁነት ላይ የተጀመሩ የትብብር ሥራዎችም የሀገሪቱን ሰላም እና ደህንነት በዘላቂነት ለማረጋገጥ፣ አቅምን ለማሳደግ እና ውጫዊ ስጋቶችን ለመከላከል የሚያስችል አስተዋጽኦ እያበረከቱ ይገኛሉ።
በኢትዮጵያና በሩሲያ መካከል እየተጠናከረ የመጣው ሁለገብ ትብብር የሁለቱን ሀገራት ታሪካዊ ወዳጅነት ወደ አዲስ ምዕራፍ የሚያሸጋግር ከመሆኑም በላይ የጋራ ብልጽግናን የሚያፋጥን ነው።
በትዝታ መንግስቱ