AMN- ጥቅምት 20/2019 ዓ.ም
ግርማ ሙሴ የተባለው ተጠርጣሪ የተለያዩ ሀሰተኛ ሰነዶችን አዘጋጅቶ ለተጠቃሚ ግለሰቦች ለመሸጥ ሲንቀሳቀስ በለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ወረዳ 8 እፎይታ አካባቢ ጥቅምት 19 ቀን 2019 ዓ.ም በቁጥጥር ስር ውሏል።
በለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ፖሊስ ዋና መምሪያ የሲ.ኤም.ሲ አካባቢ ፖሊስ መምሪያ የወንጀል ምርመራ ምክትል መምሪያ ተወካይ ኃላፊ ኢንስፔክተር ሚሊዮን የምሩ፣ ተጠርጣሪው ግለሰብ የተለያዩ ሀሰተኛ ሰነዶችን እንደሚያዘጋጅ በምርመራ ጥናት መደረጉን ገልፀዋል፡፡
የመምሪያው የክትትልና ኦፕሬሽን አባላትም ግለሰቡ ያዘጋጀውን ሀሰተኛ ሰነድ ይዞ ለተጠቃሚዎች ለመስጠት ሲንቀሳቀስ በቁጥጥር ስር በማዋል በፍርድ ቤት የመበርበሪያ ትዕዛዝ በመኖሪያ ቤቱ ብርበራ መደረጉን ተናግረዋል፡፡
በተደረገው ብርበራም ሀሰተኛ የትምህርት ማስረጃዎች፣ የተለያዩ ተቋማት ሀሰተኛ ሰነዶች፣ የተለያዩ መታወቂያዎች፣ መንጃ ፈቃድ፣ ክብና የራስጌ ማህተም፣ ቲተሮች እንዲሁም ለወንጀል ተግባሩ የሚጠቀምበት ሁለት ከለር ፕሪንተር አንድ ላፕቶፕና የተለያዩ ፍላሾች በተጨማሪም በብርና በዶላር መጠን የተዘጋጁ ሀሰተኛ የገንዘብ ኖቶች፣ ቱርክ ሰራሽ ሽጉጥ ከመሰል 11 ጥይት ጋር የተገኘ መሆኑንም አብራርተዋል።
በተጠርጣሪው ላይ ተገቢውን የምርመራ መዝገብ በማደራጀት ለአቃቤ ህግ ለማቅረብ ጉዳዩ በምርመራ ሂደት ላይ እንደሚገኝም ገልፀዋል።
ሀሰተኛ ሰነድ ማዘጋጀትም ሆነ መገልገል የህግ ተጠያቂነትን የሚያስከትል ሲሆን፣ በተለይ ሀሰተኛ ሰነድ በመጠቀም በመንግስትና በግል ተቋማት ተቀጥሮ ለመስራት መሞከር በራሱ የሚያደርሰው ጉዳት ከፍተኛ መሆኑን በመረዳት በዚህ ተግባር የተሰማሩ ግለሰቦችም ሆኑ የሚያሰሩ አካላት በአቋራጭ ለመክበር ከሚያደርጉት እንቅስቃሴ ሊታቀቡ እንደሚገባ ኢንስፔክተር ሚሊዮን የምሩ አስገንዝበዋል፡፡
ተቋማትም በሀሰተኛ ሰነድ የሚቀጠሩ አካላትን የመለየት ተግባራቸውን አጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል ሲሉ በመልዕክታቸው ማስተላለፋቸውን ከአዲስ አበባ ፖሊስ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።