AMN- ጥቅምት 20/2019 ዓ.ም
የኢትዮጵያ የባሕር በር ተጠቃሚነት ጥያቄ በሰላማዊ መንገድና በንግግር እንዲፈታ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ የድርጅቱ ዋና ጸሐፊ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ጉዋንግ ኮንግ ገለጹ።
ልዩ መልዕክተኛው አዲስ አበባን ጨምሮ በምሥራቅ አፍሪካ ቀጣና ሰላምና ደኅንነት ረገድ ኢትዮጵያ ወሳኝ ሚና የምትጫወት መልሕቅ ሀገር መሆኗን አጽንኦት ሰጥተዋል።
በአፍሪካ የሰላም መንገዶች፣ የኢኮኖሚ ሉዓላዊነትና የጂኦ-ፖለቲካ ለውጥ በሚል መሪ ሐሳብ 12ኛው የጣና ፎረም በባሕር ዳር ከተማ በስኬት ተጠናቋል።
መድረኩ የአፍሪካ ሀገራት የአሁንና የቀድሞ መሪዎችን፣ ምሁራንና ፖሊሲ አውጭዎችን ያሰባሰበ ሲሆን፤ ተሳታፊዎችም ኢትዮጵያ ለቀጣናው ሰላምና ደኅንነት ላደረገችው አበርክቶ አድናቆታቸውን ገልጸዋል።
ልዩ መልዕክተኛው ጉዋንግ ኮንግ እንዳሉት፤ የጣና ፎረም ቀጣናዊ፣ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ተቋማት በአፍሪካ ጉዳዮች ላይ የሚወያዩበት፣ እንዲሁም ልዩ መልዕክተኞች በቀጣናው ሰላምና ጸጥታ ዙሪያ ምልከታቸውን የሚለዋወጡበት ትልቅ መድረክ ነው።
ኢትዮጵያ እንደዚህ ያሉ አህጉራዊ ጠቀሜታ ያላቸው የሰላም መድረኮችን በማዘጋጀቷ ትልቅ ምሥጋናና ክብር እንደሚገባላትም አንስተዋል።
አክለውም አፍሪካውያን ሀገራትና ተቋማት ለቀጣናው ሰላም በሚበጁ ጉዳዮች ላይ በመወያየት ለችግሮች የመፍትሔ ቁልፍ መቅረጽ እንዳለባቸው አሳስበዋል።
ከዚህ አንጻር ኢትዮጵያ በሰላም ማስከበር፣ የውይይት መድረኮችን በማዘጋጀት እና የስምምነት አጀንዳዎችን አቅርቦ በማደራደር ገንቢ ሚና እየተወጣች መሆኑን ገልጸዋል።
ለአብነትም በደቡብ ሱዳን የተከሰተው ግጭት በሰላማዊ መንገድ በንግግር እንዲቋጭ ከስምምነቱ መፈረም በፊት የነበራትን ገንቢ ተሳትፎ አንስተዋል።
ኢትዮጵያ ከ130 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ያላት፣ ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት የምታስመዘግብ እና ለቀጣናው ሰላም ዋስትና የሆነች ሀገር መሆኗን የገለጹት መልዕክተኛው፤ ሀገራት የባሕር በር ተጠቃሚነታቸው የሚረጋገጥበት ዓለም አቀፍ ሕግ መኖሩን ጠቅሰዋል፤ ኢትዮጵያም ይህንን መብት በሰላማዊ ውይይት ማግኘት እንዳለባት አሳስበዋል።
በቀጣናው ያለው ውጥረት መርገብ አለበት ያሉት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ጉዋንግ፤ የባሕር በር ተጠቃሚነት በሰላማዊ ውይይት እንዲቋጭ ድጋፍ እንደሚያደርጉ መግለፃቸውን ኢዜአ ዘግቧል።