7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የኢትዮጵያ ህዝብ የራሱን እጣ ፈንታ በራሱ እጅ የጻፈበት ታሪካዊ ምዕራፍ ነው

You are currently viewing 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የኢትዮጵያ ህዝብ የራሱን እጣ ፈንታ በራሱ እጅ የጻፈበት ታሪካዊ ምዕራፍ ነው

AMN – ሰኔ 1/2018 ዓ.ም

በኢትዮጵያ የተካሄደው ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ እስከ እኩለ ሌሊት ድረስ የዘለቀ ከፍተኛ የሕዝብ ተሳትፎ፣ ታማኝነት እና ጽናት የታየበት ስኬታማ የምርጫ ሂደት እንደነበር የአገር ውስጥና ዓለም አቀፍ ታዛቢዎች ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል።

ምርጫው የኢትዮጵያ ሕዝብ የሥልጣን ሉዓላዊ ባለቤትነቱን ያረጋገጠበት እና የአገሪቱን የዲሞክራሲ ተቋማት ግንባታ ወደ አዲስ ምዕራፍ ያሸጋገረ መሆኑን የፖለቲካ ሳይንስ ተመራማሪው አቶ ሰለሞን ተፈራ ከኤ ኤም ኤን ጋር ባደረጉት ቆይታ አስገንዝበዋል።

ተመራማሪው በሰጡት ማብራሪያ፤ አንድን ምርጫ ውጤታማ ነው ለማለት ሂደቱን በቅድመ-ምርጫ፣ በምርጫ ዕለት እና ከምርጫ በኋላ ባሉ ሦስት ዋና ዋና ምዕራፎች ከፍሎ ማየት እንደሚያስፈልግ ያነሳሉ።

የመጀመሪያው ምዕራፍ የቅድመ-ምርጫ ሂደት ሲሆን አጠቃላይ ሂደቱም ፍጹም ዲሞክራሲያዊ እንደነበር ገልጸዋል።

በዚሁ ወቅት የተለያዩ አካላት ሕዝቡ ድምጽ ለመስጠት እንዳይመዘገብ ተፅዕኖ ለማሳደር ቢሞክሩም፣ በኢትዮጵያ የታሪክ ማህደር ታይቶ በማይታወቅ መልኩ ወደ 54 ሚሊዮን የሚጠጋ ሕዝብ መመዝገቡ ትልቅ ታሪካዊ አሻራ ጥሎ ማለፉን ገልጸዋል።

ከዚህ በተጨማሪም የፖለቲካ ፓርቲዎች የራሳቸውን ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊ፣ የትምህርት እና የውጭ ጉዳይ ፖሊሲዎቻቸዉን ለሕዝብ በነፃነት ያቀረቡበትና ሕዝቡም በንቃት የተሳተፈበት ምዕራፍ እንደነበር አብራርተዋል።

ሕዝቡ የቀረቡለትን አማራጮች በነፃነት በመገምገም የሀገር አደራውን ለማን እንደሚሰጥ በሙሉ ነፃነት የወሰነበት ሂደት አጠቃላይ ምርጫውን ፍትሐዊ፣ አሳታፊ እና አካታች ያደርገዋል ብለዋል።

የምርጫውን ዕለት አስመልክቶ አቶ ሰለሞን እንደገለጹት፣ የአገሪቱ ታሪካዊ ጠላቶችና ተላላኪዎቻቸው አትምረጡ በማለት የፍርሃት ድባብ ለመፍጠር ቢሞክሩም፣ ሕዝቡ ግን ያለምንም ስጋት ፀሐይና ብርድ ሳይበግረው እስከ እኩለ ሌሊት ድረስ በሰልፍ በመቆም ድምፁን ሰጥቷል።

ይህ ድርጊት መራጩ ሕዝብ የኢትዮጵያን የነገ ዕጣ ፈንታ በራሴ እጅ እጽፋለሁ ብሎ የወሰነበት ታላቅ የታሪክ ምዕራፍ መሆኑንም ጠቁመዋል።

ይህ ምርጫ ለሃገሪቱ የወደፊት ጉዞ ትልቅ የመሠረት ድንጋይ ጥሎ ማለፉን የገለጹት ተመራማሪው፣ ሕዝቡ እስከ እኩለ ሌሊት ቆሞ የመረጠው በቃሉ መሠረት ለውጥ እንዲመጣ በመሆኑ፣ አሸናፊው አካል የገባውን ቃል ቆጥሮ በመፈጸም የሕዝቡን ሕይወት የሚቀይር ሥራ መሥራት እንዳለበት አሳስበዋል።

በሌላ በኩል የምርጫ ሂደቱን መጀመሪያ ላይ በጥርጣሬ ይመለከቱ የነበሩ አንዳንድ አካላትና ተቋማት፣ የኢትዮጵያን ምርጫ ሰላማዊነትና አካታችነት በተጨባጭ ለመመስከር መገደዳቸውን አብራርተዋል።

በዚህም የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ እይታ ሊቀየር መቻሉንና ኢትዮጵያና ሕዝቧ ማሸነፋቸውን መስክረዋል ብለዋል።

ተመራማሪው አክለውም፣ ከዚህ በፊት የነበሩ የዲሞክራሲ ተቋማት ለአንድ ፓርቲ ብቻ የሚያደሉና ደካማ የነበሩ ሲሆን፣ በዚህ ምርጫ ግን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሕዝብ ሙሉ በሙሉ ያመነበትና እውነተኛ መሆኑን በተግባር አስመስክሯል።

ይህ ታሪካዊ ሂደት የፍትሕና የዲሞክራሲ ተቋማት ግንባታ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ መምጣቱን ያሳየ መሆኑን የጠቀሱት አቶ ሰለሞን፣ ከዚህ በኋላ በኢትዮጵያ ውስጥ በጠመንጃ ኃይል የሚመጣን ሥልጣን ሕዝቡ በፍጹም የማይቀበለው መሆኑ በተጨባጭ የተረጋገጠበት ነው።

በበረከት ጌታቸው

See less

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review