AMN- መስከረም 25/2019 ዓ.ም

ኢትዮጵያ ረጅም የሀገረ መንግስት ግንባታ ታሪክ ያላት ብትሆንም፣ በሒደቱ በርካታ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ውጣ ውረዶችን አሳልፋለች።
ያለፉት ሥርዓቶች በብሔራዊ ትርክት፣ በማዕከላዊና ክልል የሥልጣን ሚዛን፣ በፖለቲካ ምህዳሩ አካታችነት እና በስልጣን ሽግግር ረገድ ከፍተኛ ክፍተቶች ነበሩባቸው።
ልዩነቶችን በውይይት ከመፍታት ይልቅ ኃይልንና ማግለልን መምረጥ፣ እንዲሁም ስልጣንን በኃይል ለመያዝ የሚደረጉ ጥረቶች ሀገሪቱን ለጦርነትና ለድህነት አዙሪት ዳርገዋታል።
በተቃራኒው፣ በቅርብ ዓመታት የተደረጉ ጥረቶች እነዚህን የረጅም ዘመን ስብራቶች ለመጠገንና የሚከተሉትን አዎንታዊ እርምጃዎች ለመውሰድ አስችለዋል፡፡
ብዝሃነት የግጭት ሳይሆን የልማትና የሰላም ጸጋ እንዲሆን የማድረግ፣ እንዲሁም የጽንፈኝነት እሳቤዎችን በወንድማማችነት የመተካት ስራዎች ተከናውነዋል።
ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር፣ በምርጫ የሚመሰረት መንግስት እና ልዩነቶችን በምክክር የመፍታት ባህል እየተገነባ ይገኛል።
ገለልተኛ የሆኑ የመከላከያ፣ የደህንነት እና የአገልግሎት ሰጪ ተቋማት መሰረት ተጥሏል።
እንደ ታላቁ ህዳሴ ግድብ ያሉ ሜጋ ፕሮጀክቶች ሁሉንም ዜጎች ያሳተፈ ፍትሃዊ ተጠቃሚነትን እያረጋገጡ ነው።
ሀገሪቱን ከመልክዓ ምድራዊ እስረኝነት ነጻ ለማውጣትና ኢኮኖሚያዊ ስብራትን ለመጠገን ብርቱ ጥረት እየተደረገ ይገኛል።
በአጠቃላይ፣ በአሁኑ ወቅት እየተገነባ ያለው የመደመር መንግሥት ያለፉትን ስብራቶች በማከም ኢትዮጵያን በቀጣናውና በአፍሪካ ልዕለ-ኃያል ሀገር የማድረግ ርዕይ የሰነቀ ነው።
በወንድማገኝ አሰፋ