የቆሻሻ አወጋገድ ሥርዓትን ከታዳሽ ኃይልና ከተፈጥሮ ተስማሚ ልማት ጋር በማስተሳሰር የአካባቢ ብክለትን መቀነስ ተችሏል

AMN- ነሐሴ 7/2018 ዓ.ም

በአዲስ አበባ የቆሻሻ አወጋገድ ሥርዓትን ከታዳሽ ኃይልና ከተፈጥሮ ተስማሚ ልማት ጋር በማስተሳሰር ከተማዋን ለኑሮ ተስማሚና ውብ ማድረግ ተችሏል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ ጽዳት አስተዳደር ኤጀንሲ መረጃ እንደሚያመለክተው፣ የደረቅ ቆሻሻ አስተዳደር ሥርዓቱን በማዘመን ከተማዋ በአፍሪካ በጽዳታቸው ከተመሰከረላቸው 10 ከተሞች አንዷ ለመሆን በቅታለች።

የሕዝብ ቁጥር መጨመር የሚያስከትለውን የቆሻሻ ክምችት በዘላቂነት ለማስተዳደርም በረጲ የደረቅ ቆሻሻ ማስወገጃ በተለምዶ ቆሼ የሚሰበሰበው ቆሻሻ ለኃይል ማመንጫነት እየዋለ ይገኛል።

በአፍሪካ ቀዳሚ የሆነው የረጲ የቆሻሻ ኃይል ማመንጫ ጣቢያ፤ ደረቅ ቆሻሻን በማቀናበር ወደ ኤሌክትሪክ በመቀየር በቀጥታ ወደ ብሔራዊ የኃይል መረብ እያስገባ ይገኛል።

ይህ ጣቢያ የከተማዋን የኤሌክትሪክ ፍላጎት ከመደገፉ ባሻገር፣ ስፍራው አደገኛ የሆነውን ሚቴን ጋዝ እንዳያመነጭ በማድረግ ለአካባቢ ጥበቃ ትልቅ አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው።

ቆሻሻን ለኃይል ማመንጨት በመዋሉ ምክንያት አዳዲስ የቆሻሻ መጣያ ቦታዎችን የማዘጋጀት አስፈላጊነት የቀረ ሲሆን፣ ይህም ቀደም ሲል ለቆሻሻ መጣያነት ይባክን የነበረውን መሬት ለተለያዩ የልማት ሥራዎች ለማዋል የሚያስችል ዕድል ፈጥሯል።

ኅብረተሰቡን በጽዳት ሥራው በማሳተፍም ቀደም ሲል ለብክለትና ለደህንነት ሥጋት ተጋላጭ የነበሩ የቆሻሻ ማከማቻ ስፍራዎች አሁን ላይ ተለውጠው ለነዋሪዎች ምቹና ማራኪ ወደሆኑ የመዝናኛ ቦታዎች ተቀይረዋል።

የከተማዋን ፅዳትና ውበት ከመጠበቅ ጎን ለጎን ደረቅ ቆሻሻን በአግባቡ በመያዝ ወደ ሀብት በመቀየር ሂደቱ፣ ለበርካታ ወጣቶችና ሴቶች ሰፊ የሥራ ዕድል መፍጠር አስችሏል።

የረጲ ፕሮጀክት የቆሻሻ አወጋገድ ሥርዓትን ከታዳሽ ኃይልና ከተፈጥሮ ተስማሚ ልማት ጋር በማስተሳሰር የአካባቢ ብክለትን በመቀነስ አዲስ ምዕራፍ ከፍቷል፡፡

ይህ ስኬት ለአዲስ አበባ ብቻ ሳይሆን፣ ለሌሎች የአፍሪካ ዋና ዋና ከተሞችም ትልቅ ተሞክሮ ሆኖ እያገለገለ ይገኛል።

በበረከት ጌታቸው

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review