ዓባይን ያጋራች ኢትዮጵያ ቀይ ባህርን የመጋራት መብት አላት

AMN – ጥቅምት 1/2019 ዓ.ም

ኢትዮጵያ የጋራ ተጠቃሚነት የሚለውን ዘመናዊና ስልጡን መንገድ መመሪያዋ በማድረግ ተፈጥሯዊ ሀብቶቿ ለጋራ ልማት እንዲውሉ ስትተባበር ቆይታለች። ለዚህ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታና አሠራር ጉልህ ማረጋገጫ ይሆናል።

ኢትዮጵያ ከ85 በመቶ በላይ የሚሆነው የዓባይ ወንዝ ውሃ አመንጭ ሀገር ብትሆንም፣ ሀብቱን ሙሉ በሙሉ ለብቻዋ ልጠቀም አላለችም። የታችኞቹን የዓባይ ተፋሰስ ሀገራት ጥቅም ባልጎዳና የጋራ እድገትን በሚያፋጥን መልኩ ግድቡን ገንብታ ለምረቃ አብቅታለች።

ኢትዮጵያ ከምታመነጨው ታዳሽ የኤሌክትሪክ ኃይል እንደ ሱዳን ፣ ጂቡቲና ኬንያ ላሉ ጎረቤቶቿ በቅናሽ ዋጋ በማቅረብ የቀጣናውን ኢኮኖሚያዊ ትስስር እያጎለበተችም ትገኛች። ወንዞቿን የትስስር፣ የልማትና የሰላም ድልድይ በማድረግ ለጎረቤቶቿ አጋሪ መሆኗን በተግባር አሳይታለች።

በአንጻሩ በርካታ የሕዝብ ቁጥር ያላት ፣ በምሥራቅ አፍሪካ ፈጣን እድገት የምታስመዘግብ እንዲሁም የዓለም አቀፍ ትራንስፖርት ዐቢይ መስመር የሆነቺው ኢትዮጵያ ፣ የባህር በር እንዳይኖራት ተደርጎ መገለሏ ተፈጥሮአዊና ህጋዊ ምክንያታዊነት የለውም።

የውሃ ሀብቷን ለጎረቤቶቿ በጋራ ጥቅም የምታጋራዋ ኢትዮጵያ ፣ በቀይ ባህርና በዓለም አቀፍ የባህር መስመር የጋራ ተጠቃሚነት መብቷ ሊከበርላት ይገባል።

ኢትዮጵያ በቀይ ባህርና በኤደን ባህረ-ሰላጤ አካባቢ የሚደረገውን የንግድ እንቅስቃሴ ደህንነት በማስጠበቅ ረገድ ሰፊ አስተዋጽኦ ማበርከት የምትችል ሀገር እንደመሆኗ ፣ ከባህሩ መገለሏ የቀጣናውን ጸጥታና ደህንነት አደጋ ላይ ይጥለዋል።

ኢትዮጵያ የተፈጥሮ ሀብቷን ለጎረቤቶቿ እንዳጋራችው ሁሉ ፣ ጎረቤት ሀገራትም የተፈጥሮ ሀብት የሆነውን የባህር በርና የባህር ሀብት ለኢትዮጵያ በፍትሐዊና በጋራ ተጠቃሚነት ስምምነት ሊያጋሯት ይገባል።

ኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄዋን እያነሳች ያለችው የሌሎችን ሀገራት ሉአላዊነት በመጋፋት ወይም በኃይል ሳይሆን፣ በተመሳሳይ የጋራ ተጠቃሚነትና በሰላማዊ ውይይት መርህ ነው።

ዓባይን ለጋራ ልማት እንዲውል ያደረገች ሀገር ፣ በቀይ ባህርም ላይ ፍትሐዊ የመጋራትና የመጠቀም መብት ሊኖራት ይገባል።

የቀጣናው ሀገራት ይህን የኢትዮጵያን ተፈጥሮአዊና ምክንያታዊ ጥያቄ በመረዳት፣ በጋራ ልማትና እድገት ላይ የተመሠረተ አዲስ የታሪክ ምዕራፍ እንዲከፍቱ ይሁንታቸው ይጠበቃል።

ኢትዮጵያ ከቀይ ባህር ተገልላ ልትቆይ አትችልም ፣ የቀይ ባህር ደህንነትና ሰላምም ያለ ኢትዮጵያ ሙሉ ሊሆን አይችልም።

በታደሰ ሽፈራው

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review