AMN ሚያዚያ 27/2018 ዓ.ም
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በአማራ ክልል በትጥቅ ትግል ላይ ቆይተው ከተመለሱ አካላት ጋር ውይይት እያካሄደ ነው፡፡
የውይይት መድረኩን በንግግር የከፈቱት ዋና ኮሚሽነር መስፍን ዓርዓያ (ፕሮፌሰር) ከዘህ በፊት በተደረገ ውይይት በአማራ ክልል ታጥቀው ሲንቀሳቀሱ የነበሩና ሰላምን መርጠው የተመለሱ አካላት ክልላዊና ሀገራዊ ፋይዳቸው የጎላ 17 (አስራ ሰባት) አጀንዳዎችን ሰንደው ለኮሚሽኑ ማስረከባቸውን አስታውሰዋል፡፡

እነዚህ ወገኖች ቀደም ሲል በተደረገው ውይይት ያነሳችኋቸውን ጥያቄዎች ኮሚሽኑ ለሚመለከተው አካል ማቅረቡንም ተናግረዋል።
ይህ መድረክ ከኮሚሽኑ ጋር ይበልጥ ተቀራርባችሁ ለሰላም የምትሰረሩበት፣ የቀሩ ወገኖችን ወደ ሰላም ለማምጣት የሚያስችል ምክረሃሳብ የምትሰነዝሩበት ይሆናል ሲሉም ዓላማውን አስረድተዋል፡፡

አያይዘውም ኮሚሽኑ በምክክር ሂደቱ በሌሎች አካባቢዎች ታጥቀው የሚንቀሳቀሱ አካላትን ለማካተት እያደረገ ያለውን ጥረት አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል፡፡
የተሣታፊዎች ተወካዮች ባደረጉት ንግግር ጥያቄዎቻቸውን በኃይል ለማስመለስ ሲንቀሳቀሱ መቆየታቸውን አስታውሰው፤ የሰላም ጀግና መሆን እንደሚሻል አስረድተዋል፡፡ ምክክር የሀሳብ ልዩነቶችን የመፍቻ ብቸኛ መንገድ መሆኑን እንደሚያምኑ በመግለፅ።
ለተከታታይ ሶስት ቀናት በሚቆየው በዚህ ውይይት 200 የሚደርሱ በአማራ ክልል በትጥቅ ትግል ላይ የቆዩና አሁን ላይ ሰላምን መርጠው የተመለሱ ወገኖች እየተሳተፉ እንደሚገኙ የኮሚሽኑ መረጃ ያመላክታል፡፡
ኮሚሽኑ ጥር 28/2018 ዓ.ም በአማራ ክልል በትጥቅ ትግል ላይ ቆይተው ከተመለሱ የተወሰኑ አካላት ጋር የመጀመሪያ ውይይትና የአጀንዳ ርክክብ መድረክ ማካሄዱ አይዘነጋም፡፡