AMN- ጥቅምት 2/2019 ዓ.ም

ኢትዮጵያ በታሪኳ የውጭ ወራሪዎችን በጽናት ድል በማድረግ ከራሷ አልፋ የመላው ጥቁር ሕዝቦች የነጻነትና ተምሳሌት የሆነች ታላቅ ሀገር ናት።
የታላቅ ርዕይ ባለቤት የሆነችው ኢትዮጵያ፤ ልጆቿ ከምንጊዜውም በላይ ኅብረ-ብሔራዊ አንድነታቸውን በማጠናከር ሉዓላዊነቷንና ሁለተናዊ ልማቷን እውን ለማድረግ በጽናት ቆመዋል።
የበርካታ የተፈጥሮ ጸጋዎች ባለቤት የሆነችው ኢትዮጵያ ዜጎቿ ልዩነቶቻቸውን እንደ ውበትና ጥንካሬ በመጠቀም በአንድነትና በልማት የሀገራቸውን ታላቅነት ለዓለም እያስመሰከሩ ይገኛሉ።
የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማም የታላቅ ሀገር ታሪክ፣ የሕዝቦች ጽናት እና የብሩህ ርዕይ ማሳያ ሆኖ በክብር መውለብለቡን ቀጥሏል።

ሀገሪቱ ሰንደቅ ዓላማዋ በየዘመናቱ ከፍ ብሎ እንዲውለበለብ እና የሀገሪቱ ዳር ድንበር ተከብሮ እንዲኖር ያስቻለው የሀገር መከላከያ ሠራዊት ተጋድሎና መስዋዕትነት እንዲሁም የኢትዮጵያውያን የጸና ኅብረ-ብሔራዊ አንድነት ነው።

የሀገሪቱን ዳር ድንበር በማስከበርና የዜጎችን ደኅንነት በመጠበቅ ረገድ ለሀገሩ ራሱን በቁርጠኝነት ያሰለፈው የመከላከያ ሠራዊት ሚና የላቀ ነው። ሠራዊቱ ከሕዝብ ጋር ባለው ጠንካራ ትስስርና በጸና የሀገር ፍቅር የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት በአስተማማኝ ሁኔታ አስጠብቋል።
ይህም የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ የሰላም፣ የነጻነት፣ የኅብረ-ብሔራዊ አንድነትና የእድገት አርማ መሆኑን የሚያሳይ ነው።
በትዝታ መንግስቱ