አስተማማኝ መረጃ ወደ ተግባራዊ መመሪያዎች ሲቀየር ሕይወትን ይታደጋል፤ ሐብትንም ይጠብቃል- ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

AMN – ጥቅምት 3/2019 ዓ.ም

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩትን ጎብኝተዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማሕበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት ፤ ተቋሙ የተሟላ የአየር ትንበያ አገልግሎት በመስጠት ለሀገሪቱ ልማትና አቅም ወሳኝ ሥራዎችን የሚያከናውን የረጅም ዘመን ዕድሜ ያለው ተቋም መሆኑን ገልጸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማሕበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት፤ ጉብኝቱ እየተለዋወጠ ያለውን የአየር ፀባይና የአየር ንብረት ሁኔታዎችን ለመረዳትና ምላሽ ለመስጠት ያለውን አቅም ለማጠናከር ሚቲዎሮሎጂያዊ መረጃዎችን የመሰብሰብ፣ የሳይንሳዊ ምርምር እና የቴክኖሎጂ ዕድገት ያለውን የላቀ ጠቀሜታ ያረጋገጠ ሆኖ ማግኘታቸውን አብራርተዋል።

እንደ ኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት ያሉ ተቋማትን ማጠናከር እጅግ አስፈላጊ መሆኑን የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ግብርና፣ ውሃ፣ ጤና፣ አቪዬሽን እና የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራርን ጨምሮ ቁልፍ ዘርፎች የሚደገፉባቸውን አገልግሎቶች ለማሻሻል በሰው ኃይል አቅም ግንባታ፣ በዘመናዊ ቴክኖሎጂዎች እና በመረጃ መሠረተ-ልማት ላይ መዋዕለ-ንዋይ ማፍሰስ ወሳኝ መሆኑን አሳስበዋል።

በተለይም አደጋዎችን አስቀድሞ በመተንበይ፣ የትኞቹ አካባቢዎች ላይ ጣልቃ ገብነት ይበልጥ እንደሚያስፈልግ ለመወሰን፣ እንዲሁም ወቅታዊና ውጤታማ በሆነ መንገድ ለመንቀሳቀስ የቅድመ ማስጠንቀቂያ ሥርዓቶች ያላቸው ጠቀሜታ አበረታች መሆኑን ገልጸዋል።

አስተማማኝ መረጃ ወደ ተግባራዊ መመሪያዎች ሲቀየር ሕይወትን እንደሚታደግ፣ ሐብትን እንደሚጠብቅና የተሻለ ውሳኔ ለመስጠት እንደሚያግዝም ጠቅሰዋል።

ይህ ዓይነቱ ሥራ ከሳተላይት ምልከታ ያለፈ መሆኑን የጠቆሙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ፤ ሥራው መረጃዎች ተሰብስበው፣ ተቀናብረውና ተተንትነው ወቅታዊ እርምጃ ለመውሰድ እንዲያግዙ በመላ ሀገሪቱ ባሉ ጠንካራ የመረጃ መሰብሰቢያ ጣቢያዎች እና የመረጃ ማዕከላት መረብ ላይ የተመሰረተ መሆኑን አስረድተዋል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review