AMN ሐምሌ 7/ 2018 ዓ.ም

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በ5ኛ ዓመት የስራ ዘመኑ 2ኛ አስቸኳይ ስብሰባው ሁለት የተለያዩ የብድር ስምምነቶችን መርምሮ በሙሉ ድምጽ አጽድቋል፡፡

ምክር ቤቱ በ2ኛ አስቸኳይ ስብሰባው፤ በኢትዮጵያ እና በጣልያን እንዲሁም በኢትዮጵያ እና በፈረንሳይ ሪፐብሊክ መንግሥታት መካከል የተደረጉ የብድር ስምምነቶችን መርምሮ በሙሉ ድምጽ አጽድቋል፡፡

በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ተጠሪ ሚኒስትር የተከበሩ ተስፋዬ በልጅጌ (ዶ/ር) በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ መንግስት እና በጣልያን ሪፐብሊክ መንግሥት መካከል የተደረገው የ70 ሚሊዮን ዩሮ ብድር፤ ከወለድ እና ከአገልግሎት ክፍያ ነፃ የ16 ዓመት የችሮታ ጊዜን ጨምሮ በ30 ዓመታት ውስጥ ተከፍሎ እንደሚጠናቀቅ አስረድተዋል፡፡

የፕሮግራሙ ዓላማ መንግሥት በተለያዩ ዘርፎች የጀመራቸውን የማሻሻያ እርምጃዎች ለማበረታታትና ለመደገፍ እንዲቻል የቀጥታ የበጀት ድጋፍ በማድረግ ቀጣይነት ያለው ሁሉን – ዓቀፍ የኢኮኖሚ እድገት እንዲኖር የብድር ሥምምነቱ እንደሚያግዝ የተከበሩ ተስፋዬ በልጅጌ (ዶ/ር) አስረድተዋል፡፡

ከዓለም ባንክ ሶስተኛው የኢትዮጵያ የእድገት የልማት ፖሊሲ ክንውን ጋር በተጣጣመ መልኩ፤ ለዘላቂና አስተማማኝ ልማት ለኢትዮጵያ የሚሰጥ የበጀት ድጋፍ ፕሮግራም ማስፈፀሚያ ከጣሊያን ሪፐብሊክ የቀረበ ብድር ድጋፍ መሆኑን ተጠሪ ሚኒስትሩ አያይዘው ገልጸዋል፡፡
ምክር ቤቱ የህን የብድር ስምምነቱን አዋጅ ቁጥር ፤ 1438/2018 አድርጎ በሙሉ ድምጽ አጽድቋል፡፡
በተያያዘ ምክር ቤቱ በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ መንግስት እና በፈረንሳይ ሪፐብሊክ መንግስት መካከል የተደረጉ የብድር ስምምነቶችን መርምሮ አጽድቋል፡፡
በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ በልጅጌ (ዶ/ር) ከፈረንሳይ ሪፐብሊክ መንግስት በብድር የተገኘው ገንዘብ መንግሥት የጀመረውን የሀገሪቱን የመሠረተ ልማት አውታሮች የማዘመን፣ የትዕዛዝና ቁጥጥር እና የንብረት አስተዳደር ሥርዓቶችን በቴክኖሎጂ ለመደገፍ እና ለማጠናከር ቁልፍ ሚና እንዳለው አስረድተዋል፡፡
ከፈረንሳይ መንግስት ግምጃ ቤት የተገኘው ሃምሳ አራት ሚሊዮን ስድስት መቶ ሺህ ዩሮ (ዩሮ 54,600,000) ብድር፤ በዓመት 0.347% ወለድ የሚከፈልበት እና የ10 ዓመት የችሮታ ጊዜን ጨምሮ በ25 ዓመታት ጊዜ ውስጥ ተከፍሎ እንደሚጠናቀቅ የተከበሩ ተስፋዬ በልጅጌ (ዶ/ር) ገልጸዋል፡፡
የምክር ቤት አባላት በበኩላቸው፤ የብድር ስምምነቶቹ ዘላቂ የመንግሥት ልማት ግቦችን ለማሳካት እንደሚያግዙ እና የኢትዮጵያን የዲፕሎማሲ እድገት የሚያሳዩ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
የገንዘብ ሚኒስቴር ሚኒስትር አቶ አህመድ ሽዴ የብድር ስምምነቱ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አሰራሮችን ለማዘመን እና ዲጂታላይዝድ በማድረግ የኃል ስርጭትን ለማስተዳደር አንደሚያግዝ አስረድተዋል፡፡
ክቡር ሚኒስትሩ አያይዘው መንግሥት የህዝቡን የኑሮ ጫና ለማቃለል ለምግብ ዘይት፣ ለነዳጅ እና ለማዳበሪያ ድጎማ በማድረግ እንዲሁም ገበያን ለማረጋጋት ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን መግለጻቸዉን ከምክር ቤቱ ያገኘነዉ መረጃ ያመላክታል፡፡