AMN- ጥቅምት 4 /2019 ዓ.ም

ህብረተሰቡ በተደጋጋሚ ከሚያነሳቸዉ የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች አንዱ የሙስና ጉዳይ ሲሆን፣ መንግስት ለግል ጥቅማቸዉ ብለዉ በዚህ ተግባር ላይ በተሳተፉ ግለሰቦች እና አመራሮች ላይ ጠንካራ እርምጃ ሊወስድ ይገባል ሲሉ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች መጠየቃቸዉ ይታወሳል፡፡
የመደመር መንግሥትም በሃገሪቱ ዘላቂ ሰላምና ልማትን ለማረጋገጥ ከሚያከናዉናቸዉ ዘርፈ ብዙ ተግባራት ጎን ለጎን ህብረተሰቡ በተደጋጋሚ የሚያነሳቸዉን የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ለመፍታት እየሰራ መሆኑን ገልጿል፡፡
አዲስ አበባን ጨምሮ በሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች እየተተገበረ የሚገኘዉ የአንድ ማዕከል ዲጂታል የመንግስት አገልግሎት ሙስናና ብልሹ አሰራሮችን ከመቅረፉም ባሻገር ህብረተሰቡ ግልጽና ቀልጣፋ የመንግስት አገልግሎት በቅርበት እንዲያገኝ አስችሎታል፡፡
ከዚሁ ጎን ለጎን በሙስናና ብልሹ አሰራሮች ላይ የተሳተፉ አገልግሎት ሰጪዎችን ተጠያቂ እያደረገ መሆኑን ነዉ መንግስት የገለጸዉ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባካሄደዉ 1ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 1ኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ ያረጋገጡትም ከአመራሩ ጀምሮ ሁሉም የመንግስት አገልግሎት ሰጪዎች ከሙስና በጸዳ መንገድ ህብረተሰቡን በታማኝነት ማገልገል እንደሚጠበቅባቸዉ ነዉ፡፡
የመደመር መንግሥት ካቢኔ ብቃትን፣ የሕዝብን አደራ መሸከምን፣ ሙስናን መጸየፍን እና ሁሉን አቀፍ ስብጥርን ዋነኛ መስፈርት አድርጎ በአዲስ አደረጃጀት መዋቀሩም ይህንኑ የሙስናን ጉዳይ ይበልጥ ታሳቢ ያደረገ መሆኑን የሚያመላክት ነዉ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አዲስ የተሾሙ ሚኒስትሮች ከሙስናና ሌብነት የጸዱ መሆናቸውን ለማረጋገጥ ቢያንስ ባለፈው አንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ በሀገር ውስጥና በውጭ ያላቸው እንቅስቃሴ፣ ከሚገናኟቸው ባለሀብቶች ጋር ያላቸው ግንኙነት ጭምር ጥብቅ የመረጃ ክትትል ሲደረግባቸው እንደነበር መግለጻቸዉም መንግስት ሙስናን ለመታገል ያለዉን ቁርጠኝነት የሚያረጋግጥ ነዉ፡፡
የካቢኔ አባላቱ እራሳቸውን ክፍት አድርገው ከመገምገማቸዉም በላይ ከአንድ ወር ለሚበልጥ ጊዜም በተደጋጋሚ ፈተናዎች የተደገፈ ጠንካራ ስልጠናዎች ተሰጥቷቸዋል ነዉ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፡፡
አንድ ሚኒስትር ራሱ ሌባ ላይሆን ይችላል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር)፤ ነገር ግን በአከባቢው ያለውን የሌብነት አዝማሚያ የመከታተልና የመቆጣጠር ከፍተኛ ኃላፊነት እንዳለበት ነው ያሳሰቡት፡፡
ሹመት ድሎት ሳይሆን በልፋትና በትጋት ሀገርን ማገልገል ስለሆነ፣ አመራሩ እጁም ልቡም ንጹህ ሆኖ በታማኝነትና በቁርጠኝነት ሀገሩን ሊያገለግል ይገባል፡፡
የተሾሙት የካቢኔ አባላት ህዝብ የጣለባቸውን ኃላፊነት በአግባቡ የማይወጡ ከሆነ እርምጃ እንደሚወሰድ ያረጋገጡት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ስልጣን ኮፍያ ነው፤ ጭንቅላት አይደለም፤ አስፈላጊ ከሆነ በክብር ይቀመጣል፤ አስፈላጊ ካልሆነ ደግሞ ይነሳል፡፡
ሥልጣን መጥቶ የተቀመጠብን እንጂ ከእኛ ጋር የተፈጠረ ስላልሆነ እጃችንንም ልባችንንም ንጹህ አድርገን ህዝቡን ልናገለግል ይገባል፤ ሹመት ብዙ ምቾት፣ ብዙ እንቅልፍ፣ ብዙ ድሎት ያለው ሳይሆን፤ ብዙ ኃላፊነት እና ድካም ያለው ጉዳይ ነው ብለዋል፡፡
የመደመር መንግስት በምስረታዉ እለት ሙስናና ብልሹ አሰራሮችን ለመታገል ያሳየዉ ቁርጠኝነት ህብረተሰቡ በተደጋጋሚ ለሚያነሳቸዉ የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ተገቢዉን ምላሽ ይሰጣል ተብሎ ታምኖበታል፡፡
በወንድማገኝ አሰፋ