ከለውጡ ወዲህ አማራ ክልል

You are currently viewing ከለውጡ ወዲህ አማራ ክልል

AMN- ሐምሌ 25/2018 ዓ.ም

ከለውጡ በፊት የአማራ ክልል የሚገባውን ያህል የልማት ተጠቃሚ እንዳልነበረ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገልጸዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ጋር በክፍል ሁለት ባደረጉት ቆይታ፣ ከለውጡ በፊት የአማራ ክልል የሚገባውን ያህል የልማት ተጠቃሚ እንዳልነበረ፣ በእርግጥ ይህ ችግር የአማራ ክልል ብቻ ሳይሆን በኢትዮጵያ ደረጃም ማደግ ባለብን ልክ ዕድገት አለመረጋገጡን አንስተዋል፡፡

ነገር ግን ባለፉት ጥቂት ዓመታት በችግሮች ውስጥ ሆነንም በግብርና፣ በግድብ እንዲሁም በኢንዱስትሪ ዕመርታዊ ለውጥ አስመዝግበናል ብለዋል፡፡

ከመስኖ አንጻር ጥያቄ ይነሳ እንደነበር የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ለምሳሌም መገጭ 18 ዓመት ቆይቷል፣ ጎንደር ላይ ከፍተኛ የመጠጥ ውኃ ችግር አለ፣ የላይኛው ርብ እና በሌሎችም ጥያቄዎች ይነሱ እንደነበር አውስተዋል፡፡

በክልሉ የነበሩ ግድቦችን ለማጠናቀቅ ብዙ ቢሊየን ብር ወጥቶባቸው የማይናቅ ሥራ ተሠርቷል ነው ያሉት፡፡

መገጭ በመጠናቀቅ ላይ ነው በቅርቡ ሥራ ይጀምራል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ የቆየበትን ጊዜ ርዝመት፣ የሕዝቡ ጥያቄ እና ይህን ለመመለስ የተሄደበት መንገድ ከሀብትም ሆነ ከጥቅም አንጻር ከፍኛ ቁርጠኝነት የጠየቀ መሆኑን በአጽንዖት ገልጸዋል፡፡

ከግብርና ምርት አንጻር በለውጡ ማግስት የአማራ ክልል በዓመት የሚያመርተው 90 ሚሊየን ኩንታል ገደማ እንደነበር ጠቁመው፣ ግድቦች ላይ፣ ማሽነሪ ላይ፣ ማዳበሪያ ላይ በተሠራው ሥራ፣ ፓምፕ በስፋት ማስገባት በመቻሉ ይህ አሃዝ ባለፉት ዓመታት ወደ 205 ሚሊየን ማደጉን ተናግረዋል፡፡

በኢንዱስትሪ ዘርፍም፣ የባሕርዳር፣ ደብረ ብርሃን እና አረርቲ ኢንዱስትሪያል ፓርኮች የተሠሩት ብሎም ጣና በለስ የስኳር ፋብሪካ የተጠናቀቀው ከለውጡ በኋላ መሆኑን አብራርተዋል፡፡

ለሚ ሲሚንቶ ፋብሪካም በመንግሥት ከፍተኛ እገዛ ተደርጎበት ከለውጡ በኋላ መሠራቱን ጠቁመው፣ የዘይት ፋብሪካዎችና የግለሰብ ኢንዱስትሪዎች በአማራ ክልል በስፋት መሠራታቸውን ተናግረዋል፡፡

በአጠቃላይ ኢንደስትሪ ላይ ብዙ እመርታዎች መምጣታቸውን ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቆይታቸው ገልጸዋል፡፡

በዮሐንስ ደርበው

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review